Tag: movable property

በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያለ የዋስትና መብት /ረቂቅ/ አዋጅ

አዋጅ ቁጥር ……/2011

በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያለ የዋስትና መብት አዋጅ

በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያለ የዋስትና መብት አዋጅ

ዋስትናው የተጠበቀ ዘመናዊ የብድር ሥርዓት ግለሰቦችና ተቋማት ተንቀሳቃሽ ንብረታቸውን በማስያዝ ሥራ ላይ የሚውል አዲስ ካፒታል ማግኘት እንዲችሉና በሂደቱም የፋይናንስ ተደራሽነትንና ተጠቃሚነትን ለማሳደግና ለማስፋፋት የሚያስችል በመሆኑ

 

ተንቀሳቃሽ ንብረትን በዋስትና አስይዞ ብድር ማግኘት የሚቻልበትን ሥርዓት መዘርጋትና የማስፈጸሚያ መንገዱንም ቀልጣፋና ውጤታማ ማድረግ ተገቢ በመሆኑ፤

 

ለዋስትና በተያዘ ተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ በተወዳዳሪ ባለመብቶች የሚነሳ የቀዳሚነት መብትን ለመወሰን የሚያስችል አንድ ወጥና ሁሉንአቀፍ የኤሌክትሮኒክ ምዝገባ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ስለሆነ፤

 

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55/1/መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

ክፍል አንድ

ጠቅላላ

 

  1. አጭር ርዕስ

ይህ አዋጅ ‹‹የተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያለ የዋስትና መብት አዋጅ ቁጥር…./2011›› ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

 

  1. ትርጓሜ

የቃሉ አገባብ የተለየ ትርጓሜ የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ፤

1/         ‹‹የማይንቀሳቀስ ንብረት ተጓዳኝ›› ማለት ከማይንቀሳቀስ ንብረት ጋር የተያያዘ ቢሆንም እንደተንቀሳቃሽ ንብረት የሚቆጠር ሀብት ነው፤

 

2/         ‹‹የተገኘ የዋስትና መብት›› ማለት በግዑዝ ሀብት ወይም አዕምሯዊ ንብረት ላይ ያልተከፈለ ቀሪ ዋጋን ለማስፈጸም ወይም መያዣ ሰጪው በንብረቱ ላይ የባለቤትነት መብት እንዲያገኝ ለማድረግ የተፈፀመ ብድርን ለማስከፈል እንዲቻል በዚያው መጠን በንብረቱ ላይ የተገኘ የዋስትና መብት ነው፤

 

3/         ‹‹የንግድ ተቋም›› ማለት በንግድ ሕግ የተመለከተው የንግድ መደብር ነው፤

 

4/         ‹‹በሰነድ የተደገፈ ሴኩሪቲ›› ማለት ሰነዱን በያዘው ሰው ስም ወይም ለአምጪው ተብሎ የታዘዘ አክሲዮን ወይም ቦንድ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ነው፤

 

5/         ‹‹የመያዣ መዝገብ›› ማለት በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ በስምምነት ወይም ከህግ ወይም ከፍርድ የመነጨ የዋስትና መብት መረጃን መቀበያ፣ ማስቀመጫ እና ለሕዝብ ተደራሽ ማድረጊያ የኤሌክትሮኒክ ሥርዓት ነው፤

 

6/         ‹‹የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት›› ማለት የመያዣ ምዝገባ ሥርዓትን ለማስተዳደር የሚቋቋም ጽህፈት ቤት ነው፤

 

7/         ‹‹ተወዳዳሪ ባለመብት›› ማለት ገንዘብ ጠያቂ ወይም በዋስትና በተያዘ ንብረት ላይ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ ጋር ተወዳዳሪ የመብት ጥያቄ ያለው ሌላ ሰው ነው፤

 

8/         ‹‹የፍጆታ ዕቃዎች›› ማለት መያዣ ሰጪው በዋናነት ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ የቤት ውስጥ ፍጆታ የሚጠቀምባቸው ወይም ለመጠቀም ያዘጋጃቸው ዕቃዎች ናቸው፤

 

9/         ‹‹የቁጥጥር ስምምነት›› ማለት፣

ሀ)         የኤሌክትሮኒክ ሴኩሪቲዎች ዋስትናን በተመለከተ በሰነዱ አውጪ፣ በመያዣ ሰጪው እና ዋስትና ባለው ገንዘብ ጠያቂ መካከል የተደረገና አውጪው የመያዣ ሰጪው ተጨማሪ ፈቃድ ሳያስፈልገው ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ የሚሰጠውን ትዕዛዝ በቀጥታ የሚፈጽምበት የጽሑፍ ስምምነት ነው፡፡ ወይም

 

ለ)         ከተቀማጭ ሂሳብ ላይ ክፍያ የማግኘት መብትን ለማስፈጸም በፋይናንስ ተቋሙ፣ በመያዣ ሰጪው እና ዋስትና ባለው ገንዘብ ጠያቂ መካከል የተደረገና የፋይናንስ ተቋሙ የመያዣ ሰጪው ተጨማሪ ፈቃድ ሳያስፈልገው በመያዣ ሰጪው ሂሳብ ውስጥ በተቀመጠ ገንዘብ ላይ ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ የሚሰጠውን ትዕዛዝ በቀጥታ የሚፈጽምበት የጽሑፍ ስምምነት ነው፤

 

10/       ‹‹ግዑዝ ሀብት›› ማለት ገንዘብ፣ የሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድ፣ የሚተላለፍ ሰነድ እና በሰነድ የተደገፉ ሴኩሪቲዎችን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት ዕቃ ነው፤

 

11/       ‹‹ባለዕዳ›› ማለት ዋስትና ለተገባለት ግዴታ ገንዘብ የመክፈል ወይም ግዴታውን የመፈጸም ኃላፊነት ያለበት ሰው ሲሆን ለዚሁ ዋስ የሆነንም ይጨምራል፤

 

12/       ‹‹የተሰብሳቢ ሂሳብ ባለዕዳ›› ማለት የተሰብሳቢ ሂሳብን የመክፈል ግዴታ ያለበት ሰው ሲሆን፣ ለሂሳቡ ክፍያ ዋስ የሆነን ወይም በሁለተኛ ደረጃ ዋስ የሆነ ሌላ ሰውን ይጨምራል፤

 

13/       ‹‹ተቀማጭ ሂሳብ›› ማለት ከሕዝብ ተቀማጭ ገንዘብ ለመሰብሰብ ፈቃድ በተሰጠው የፋይናንስ ተቋም ውስጥ ያለ ሂሳብ ነው፤

 

14/       ‹‹መሣሪያ›› ማለት ከንግድና የፍጆታ ዕቃዎች ውጭ የሆነና መያዣ ሰጪው በዋናነት ለሥራው የሚጠቀምበት ወይም ሊጠቀምበት የያዘው ግዑዝነት ያለው ሀብት ነው፤

 

15/       ‹‹ኤሌክትሮኒክ ሴኩሪቲዎች›› ማለት ኤሌክትሮኒካዊ በሆነ መንገድ የተመዘገቡ፡ የሚተላለፉ እና በሰነድ ያልተደገፉ አክሲዮኖችና ቦንዶች ናቸው፤

 

16/       ‹‹የግብርና ምርቶች›› ማለት የበቀሉ ወይም በመብቀል ላይ ያሉ ወይም ወደፊት የሚበቅሉ ሰብሎች፣ ደንና የደን ውጤቶች፣ የቤት እንሰሳት የሚወለዱትን ጨምሮ፣ የንብና የዶሮ ዕርባታ፣ ለግብርና ሥራ ጥቅም ላይ የሚውሉ ግብአቶች ወይም በግብርና ሥራ የተመረቱ፣ ወይም በምርት ሂደት ያልተቀየሩ የሰብል ወይም የእንስሳት ምርቶችንና ሌሎች የግብርና ውጤቶችን ያጠቃልላል፤

 

17/     ‹‹የፋይናንስ ኪራይ›› ማለት አከራዩ አንድ የተወሰነ የካፒታል ዕቃን በተከራዩ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ የሚያልቅ በሁለቱ ወገኖች ስምምነት የተወሰነ ክፍያ በየተወሰነ ጊዜ በመፈጸም እንዲጠቀምበት የሚያከራይበት፣ የኪራይ ስምምነቱ ጸንቶ በሚቆይበት ጊዜ አከራዩ በካፒታል ዕቃው ላይ ሙሉ የባለቤትነት መብት ይዞ የሚቆይበትና የኪራይ ዘመኑ ሲያበቃ ሁለቱም ወገኖች ከተስማሙ ተከራዩ የካፒታል ዕቃውን ሊገዛ የሚችልበት የኪራይ ዓይነት ነው፤

 

18/       ‹‹ታሳቢ ሀብት›› ማለት ገና ያልተፈጠረ ወይም የዋስትና ስምምነቱ በሚፈጸምበት ጊዜ መያዣ ሰጪው ገና የባለቤትነት መብት ያላገኘበት ተ   ንቀሳቃሽ ንብረት ነው፤

 

19/       ‹‹መያዣ ሰጪ›› ማለት ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ግዴታ ማስፈፀሚያ ዋስትና ያስያዘ፣ በዋስትና ግዴታ የተያዘ ንብረትን ከነግዴታው የገዛ፣ የተላለፈለት፣ የተከራየ ወይም የመጠቀም ፈቃድ ያለው፣ በዱቤ ግዢ መሠረት የተከራየ ሰው ነው፤

 

20/       ‹‹የዱቤ ግዢ›› ማለት አከራይና ተከራይ ባደረጉት ስምምነት መሠረት አከራይ በተወሰነ ጊዜ የሚደረግ ክፍያ እየተከፈለው አንድ የተወሰነ የካፒታል ዕቃን ተከራዩ እንዲጠቀምበት የሚፈቅድበት፣ እያንዳንዱ ክፍያ በተደረገ ቁጥር ለክፍያው ተመጣጣኝ በሆነ መቶኛ ልክ ለተከራይ የባለቤትነት መብት የሚተላለፍበትና ተከራይ የመጨረሻውን ክፍያ እንደፈጸመም በካፒታል ዕቃው ላይ ሙሉ የባለቤትነት መብት ወዲያውኑ የሚያገኝበት የኪራይ ዓይነት ነው፤

 

21/       ‹‹ግዑዝነት የሌለው ሀብት›› ማለት ተሰብሳቢ ሂሳብን፣ ተቀማጭ ሂሳብን፣ የአእምሯዊ ንብረት መብትንና ከግዑዝ ንብረት ውጭ ያሉ ተመሳሳይ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን ያካትታል፤

 

22/       ‹‹አምሯዊ ንብረት›› በአገሪቱ አእምሯዊ ንብረት ህጎች የተሰጠው ትርጉም ይኖረዋል፡፡

 

23/       ‹‹ንግድ ዕቃ›› ማለት ጥሬ እና በከፊል የተቀነባበሩትን ጨምሮ መያዣ ሰጪው በመደበኛ የንግድ ሥራ ሒደት ለሽያጭ ወይም ለኪራይ የያዘው ግዑዝ ሀብት ነው፤

 

24/       ‹‹ውህድ ወይም ምርት›› ማለት አንድን ምርት ከሌላ ምርት ጋር በማዋሀድ ወይም በመቀላቀል የሚፈጠር አዲስ ይዘት ያለው ምርት ወይም ውህድ ነው፤

 

25/       ‹‹ገንዘብ›› ማለት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚታተሙ ሕጋዊ መገበያያ የገንዘብ ኖቶች እና የሚቀረጹ ሳንቲሞች፣ ወይም             በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈጸም ክፍያ ተቀባይነት ያላቸውና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተገለጹ የሌላ ሀገር ሕጋዊ የመገበያያ የገንዘብ ኖቶች እና ሳንቲሞች ናቸው፤

 

26/       ‹‹ተንቀሳቃሽ ንብረት›› ማለት የንግድ ዕቃዎችን፣ የግብርና ምርቶችን፣ ግዑዝነት የሌላቸው ሀብቶችን፣ ግዑዝ ሀብቶችን፣ ከመሬት፣ ከቤት ወይም ከሕንጻ ውጭ ያሉ ንብረቶችን፣ በሕግ ካልተከለከለ በስተቀር በመሬት ላይ የመጠቀም መብትን፣ በዱቤ ግዢ የሚገኝ መብት፣ በአደራ የተቀመጠ ንብረት ሠነድ፣ የአደራ መያዣ ደረሰኝ፣ የሸቀጦች ጭነት፣ ንግድን ለዋስትና ማስያዝ፣ ባለቤትነትን በማስጠበቅ የሚደረግ ሽያጭ፣ የተሸጠ ንብረትን መልሶ ለመግዛት መብት የሚሰጥ ሽያጭ፣ በምስክር ወረቀት የሚረጋገጡ ሴኩሪቲዎች ላይ የሚመሠረት የዋስትና መብት፣ እና በመጋዘን ደረሰኝ ላይ ያለ የዋስትና መብትን ያካትታል፤

 

27/       ‹‹የሚተላለፍ ሰነድ›› ማለት በሰነዱ ላይ የተገለጸውን ንብረት የመረከብ መብት የሚሰጥና ሊተላለፍ የሚችል እንደ ማጓጓዣ ሰነድ፣ ቫውቸር ወይም በመጋዘን የተቀመጠ ዕቃ መቀበያ ደረሰኝ ነው፤

 

28/       ‹‹የሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድ›› ማለት የሐዋላ ወረቀት፣ የተስፋ ሰነድ እና ከቼክ በስተቀር ሌላ ለአምጪው ወይም በስሙ ወይም ለታዘዘለት ተብሎ የተዘጋጀ ሰነድን ያካትታል፤

 

29/       ‹‹በህግ ወይም በፍርድ ገንዘብ ጠያቂ የሆነ›› ማለት በዋስትና መያዣ ላይ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወይም በሕግ ገንዘብ የመጠየቅ መብት ያገኘ ሰው ነው፤

 

30/       ‹‹ማስታወቂያ›› ማለት በዚህ አዋጅ መሠረት ዋስትና ባለው ገንዘብ ጠያቂ ወይም ፈቃድ በተሰጠው ሰው በመያዣ መመዝገቢያ ሥርዓት ውስጥ የሚካተት የመጀመሪያ ምዝገባ፣ የማስተካከያ ምዝገባ ወይም የስረዛ ምዝገባ ነው፤

 

31/       ‹‹የአጭር ጊዜ መጠቀሚያ ኪራይ›› ማለት በአከራዩ እጅ የሚገኝ አንድ የተወሰነ የካፒታል ዕቃን ተከራዩ በሁለቱ ወገኖች ስምምነት የተወሰነ ኪራይ በመክፈል ከሁለት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ እንዲጠቀምበት የሚከራይበት የኪራይ ዓይነት ነው፤

 

32/       ‹‹ቀደምት ሕግ›› ማለት ይህ አዋጅ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት በሥራ ላይ የነበረ ሕግ ነው፤

 

33/       ‹‹ቀደምት የዋስትና መብት›› ማለት ይህ አዋጅ ከመፅናቱ በፊት በተፈጸመ የዋስትና ስምምነት የተሸፈነ መብት ነው፤

 

34/       ‹‹ይዞታ›› ማለት አንድ ሰው ወይም ተወካዩ አንድን ግዑዝ ንብረት በራሱ  ወይም በሌላ ሰው ሃላፊነት ሥር እንዲሆን ማድረግ ነው፤

 

35/       ‹‹ተያያዥ ገቢ›› ማለት ከዋስትና መያዣው የሚገኝ ማንኛውም ገቢ ሲሆን፣ በሽያጭ፣ በማስተላለፍ፣ በመሰብሰብ፣ በማከራየት ወይም በፈቃድ የተገኘ ወይም የፍሬ ገቢ፣ የመድን ገቢ፣ በዋስትና ከተያዘው ንብረት ብልሽት፣ ጉዳት ወይም መጥፋት ጋር ተያይዞ የሚሰበሰብ ገቢንና በዚሁ ገቢ አማካይነት የተገኘ ተጨማሪ ገቢን ያካትታል፤

 

36/       ‹‹ተሰብሳቢ ሂሳብ›› ማለት ተንቀሳቃሽ ንብረት ሲሆን ከሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድ፣ ከተቀማጭ ሂሳብ እና ከዋስትና የሚገኝ የክፍያ መብትን ሳይጨምር ገንዘብ የመከፈል መብት ነው፤

 

37/       ‹‹የታወቀ ገበያ›› ማለት ዋጋ በይፋ የሚገለጽበት እና/ወይም በንግድ አሰራር ተገቢ ነው ተብሎ የሚታመንበት የተለመደና የታወቀ ገበያ ማለት ነው፤

 

38/       ‹‹መዝጋቢ›› ማለት ምዝገባው በሚጠይቀው መሥፈርት መሠረት መረጃዎችን በመያዣ መመዝገቢያ ሥርዓት ውስጥ የሚመዘግብ ወይም የሚያካትት ሰው ነው፤

 

39/       ‹‹ሬጅስትራር›› ማለት የመያዣ ምዝገባ ሥርዓቱን እንዲያስተዳድር እና  እንዲቆጣጠር  በመንግስት  የሚሾም ሰው ነው፤

 

40/       ‹‹መረጃ›› ማለት በመያዣ መመዝገቢያ ሥርዓት ውስጥ የተቀመጠ፣ የተጠበቀ፣ የተደራጀና ለሕዝብ ክፍት የሆነ የተመዘገበ መረጃ ነው፤

 

41/       ‹‹ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ›› ማለት           የዋስትና መብት ያለው ወይም           በህግ ወይም በፍርድ የገንዘብ ጠያቂነት መብት የተሰጠው ሰው ነው፤

 

42/       ‹‹የዋስትና ስምምነት›› ማለት ተዋዋይ ወገኖች የዋስትና ስምምነት ብለው ባይሰይሙትም በመያዣ ሰጪውና በመያዣ ተቀባዩ መካከል የተፈረመ የዋስትና መብት የሚፈጥር ስምምነት ነው፤

 

43/       ‹‹የዋስትና መብት›› ማለት ተዋዋይ ወገኖች የዋስትና መብት ብለው ባይሰይሙትም በንብረቱ ዓይነት፣ በመያዣ ሰጪውና ተቀባዩ እና ዋስትና በተገባለት ግዴታ ላይ ሳይወሰን የክፍያ ወይም ሌላ ግዴታን ለማስፈጸም በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የሚፈጠር መብት ነው፤

 

44/       ‹‹መለያ ቁጥር›› ማለት በሻሲ ወይም በሌላ የፋብሪካ ምርት አካል ላይ የሚገኝ መለያ ቁጥር ነው፤

 

45/       ‹‹መለያ ቁጥር ያለው መያዣ›› ማለት በአምራቹ በቋሚነት የተጻፈ ወይም የተለጠፈ መለያ ቁጥር ያለው ሞተር ተሽከርካሪ፣ ተሳቢ፣ የእርሻ መሣሪያ፣ የኮንስትራክሽን መሣሪያ፣ የኢንዱስትሪ መሣሪያ እና ሌላ መለያ ቁጥር ያለው ዕቃ ነው፤

 

46/       ‹‹ሰው›› ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፤

Continue reading “በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያለ የዋስትና መብት /ረቂቅ/ አዋጅ”