Tag: judgement writing

‘እንዳልተሰጠ የሚቆጠር ውሳኔ’ ምን ዓይነት ነው?

በህግ አግባብ የተቋቋመ ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን አከራክሮ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ለአፈጻጸም ሲቀርብ ውሳኔው እንዳልተሰጠ ተቆጥሮ አፈጻጸሙን በያዘው ፍርድ ቤት ዋጋ የሚያጣበት የህግ መሰረት አለ? ከሰበር ችሎት ውሳኔዎች ለመረዳት እንደሚቻለው አንድ ውሳኔ በሶስት መንገዶት እንዳልተሰጠ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የስረ ነገር የዳኝነት ስልጣን አለመኖር ነው፡፡ ምንም እንኳን ችሎቱ በአንድ መዝገብ ላይ ይህን አቋም ቢያራምድም በሌሎች ሁለት መዝገቦች ላይ ግን ራሱን በመቃረን የስረ ነገር የዳኝነት ስልጣን የፍርድ ቤትን ውሳኔ እንዳልተሰጠ እንደማያስቆጥረው የህግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ሌሎቹ ሁለት መንገዶችና የችሎቱ ተቃርኖ የታየባቸው መዝገቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡

  1. የሥረ ነገር የዳኝነት ስልጣን በሌለው ፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ

አንድ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ከማየቱ በፊት የስረ ነገር የዳኝነት ስልጣን ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ያለበት ሲሆን የስረ ነገር የዳኝነት ስልጣን በተከራካሪ ወገኖች ባይነሳም በማናቸውም የክርክር ደረጃ ፍርድ ቤቱ በራሱ ሊያነሳው የሚገባው ጉዳይ መሆኑ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 9 እና 231/1/ ሰ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዲይ ነው፡፡ የሥረ ነገር የዳኝነት ስልጣን በሌለው ፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ ደግሞ በመርህ ደረጃ እንዳልተሰጠ የሚቆጠር ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 64703 ቅጽ 12፣[1] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 9፣ 231/1/ ሰ

  1. ችሎት ለማስቻል በህጉ የተቀመጠው የዳኞች ቁጥር ባልተሟላበት ሁኔታ የሚሰጥ ውሳኔ

ጉዳዮች በሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት የሚመሩበት አይነተኛ አላማ ክርክሮችን ፍትሃዊ በሆነ እና ሥርዓት ባለው መንገድ በመምራት በአጭር ጊዜ እና በአነስተኛ ወጭ እንዲቋጩ ማድረግ ስለመሆኑ ይታመናል፡፡ ይህንኑ የሥነ ሥርዓት ሕጉን አላማ ለማሳካት ደግሞ በሕጉ የተመለከቱትን የስነ ሥርዓት ድንጋጌዎችን እንደየአግባብነታቸው መከተልን የግድ ይላል፡፡ በስነ ሥርዓት ሕጉ የተመለከቱት ድንጋጌዎችን እንደየአግባብነታቸው ያለመከተል በተከራካሪ ወገኖች መሰረታዊ መብት ላይ አሉታዊ ውጤት ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ስለሆነም በስነ ስርዓት ሕጉ የተመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት ሊኖራቸው የሚገባው ለጉዳዩ አግባብነት ሲኖራቸው እንጂ በዘፈቀደ ሊሆን አይገባም፡፡

ድንጋጌዎቹ አግባብነት ያላቸው ስለመሆኑ ከመለየቱ በተጨማሪ በጉዳዩ ላይ ተገቢነት አለው የሚለውን ትዕዛዝ ወይም ውሣኔ የሚሰጠው ችሎትም በሕጉ አግባብ የተመለከተው የዳኞች ቁጥር የተሟላ ሊሆን ይገባል፡፡ በሕጉ አግባብ ሊሟላ የሚገባው የዳኞች ቁጥር ሳይሟላ የሚሰጠው ትእዛዝ ወይም ውሣኔ እንደተሰጠ የማይቆጠርና ሕጋዊ ውጤት ሊኖረው የሚገባ አይደለም፡፡

ሰ/መ/ቁ 73696 ቅጽ 13[2]

  1. በሞተ ሰው ውክልና ክርክር ተደርጎ የተሰጠ ውሳኔ

በሞተ ሰው ስም ቀደም ብሎ የተሰጠን ውክልና በመያዝ የሚቀርብ ክስ፣ የሚደረግ ክርክር እና የሚሰጥ ውሣኔ ህጋዊ ዕውቅናና ውጤት ሊሰጠው የማይገባው ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 95587 ቅጽ 17፣[3] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 57፣ ፍ/ህ/ቁ. 2232/1/

ከሰ/መ/ቁ. 64703 ጋር ተቃርኖ

አንድ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ በሕግ ከተሰጠው የስረ ነገር የዳኝነት ስልጣን ውጭ የሆነ ጉዳይ በማየት የሰጠው ቢሆንም፣ ይህ ውሣኔ በይግባኝ ታይቶ እንዲታረም ካልተደረገ በስተቀር በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 212 በጉዳዩ ላይ አስገዳጅነት ያለውና የመጨረሻ ውሣኔ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 85718 ቅጽ 15[4]

በሕግ አግባብ በፍ/ቤት የተሰጠን ውሣኔ የሞራልን ወይም የሕሊናን አስተሳሰብ መሠረት በማድረግ ዋጋ አልባ ሆኖ እንዲቀር ማድረግ በየትኛውም መለኪያ ተቀባይነት የሚኖረው አይደለም፡፡

ሰበር መ/ቁ. 38041 ቅጽ 8[5]

[1] አመልካች ሻምበል ለታይ ገ/መስቀል እና ተጠሪ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳ 1 አስተዳደር ጽ/ቤት ሐምሌ 29 ቀን 2003 ዓ.ም.

[2] አመልካች ወ/ሪት ሃና አበባው እና ተጠሪ አቶ አብዱ ይመር /በሌለበት/ ሚያዝያ 9 ቀን 2004 ዓ.ም.

[3] አመልካች ወ/ሮ ሐዋ በከር እና ተጠሪ እነ አቶ ቶፊቅ መሀመድ 2 ሰዎች ጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ.ም.

[4] አመልካች አቶ ቴዎድሮስ አማረ እና ተጠሪ አቶ አዲሱ ፍሰሃ ሰኔ 03 ቀን 2005 ዓ.ም.

[5] አመልካች ታደሰ ገ/መስቀል ተጠሪዎች እነ ሙሉጌታ ዘካርያስ /7 ሰዎች/ መጋቢት 22 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም.

‘ሰድቦ ለሰዳቢ’፡ በፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ የፀያፍ ቃላት አገላለጽ

በእኛ አገር ‘ተሰደብኩኝ ስሜ ጠፋ’ ብሎ ለፖሊስ የሚያመለክት ሰው አንድም አልታደለም አሊያም አዙሮ አላሰበም፡፡ ወደ ፖሊስ ያመራው በሰው ፊት ሲሰደብ፣ ስሙ ሲጠፋ መጠቃቱ አንገብግቦት፣ በንዴት ሰክሮ ባስ ሲልም ራሱን መቆጣጣር አቅቶት ይሆናል፡፡ ክብሩ ተነክቷልና ይሄ ጥጋበኛ ሰዳቢ በፍትሕ ፊት ቀርቦ የእጁን ማግኘት አለበት፡፡ ተሰደብኩኝ ባይ ወደ ፖሊስ በማምራት አንዴ የጠፋ ስሙን ለማደስ ባይችልም በእርግጥም ፍትሕ ያገኝ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ከሚያገኘው ይልቅ የሚያጣው ነገር ይበልጣል፡፡

በመጀመሪያ ‘እከሌ እንዲህ ብሎ ሰደበኝ’ የሚል ማመልከቻ ይዞ ፖሊስ ጣቢያ ሲሄድ ይህ ማመልከቻው በትንሹ በ3 እና 4 ፖሊስ እይታ ውስጥ ይገባል፡፡ ስድቡ ለጆሮ የሚዘገንን ወይም ቃላቶቹና አገላለጻቸው በአካባቢው ከተለመደው የተለየና ወጣ ያለ ከሆነ መርማሪው ፖሊስ እንዲሁም ማመልከቻውን ያነበቡ ፖሊሶች ወሬውን በጨዋታ መልክ ለሌሎች ፖሊሶች ሹክ ማለታቸው አይቀርም፡፡ አስቂኝ ይዘት ካለው ደግሞ የወሬ ቅብብሎሹ እስከ ዕለቱ ተረኛ ፖሊሶች ድረስ ይዛመታል፡፡

ቀጥሎ ባለው ሂደት ፖሊስ የምርመራ መዝገብ ይከፍትና ማመልከቻውም ከግላዊ ወደ መንግስታዊ ሰነድነት ይሸጋገራል፡፡ አመልካች በለስ ቀንቶት ከጊዜ በኋላ ሹመት ቢያገኝ፣ ዝና ቢቀዳጅ ፖሊስ የእርሱን ማመልካቻ አውጥቶ አይቀደውም፡፡ መዝገቡን ለአዲሱ ስሙ ሲል አያጠፋውም፡፡ በቃ! ሁሌ እዛው ነው፡፡

በምርመራ መዝገቡ ውስጥ የአመልካች ቃል እና የምስክሮች ቃል ይሰፍራል፡፡ የምስክሮችን ብዛት በትንሹ በሁለት ብንወስነው አመልካችን ያንገበገበው የስድብ ቃል ሶስት ጊዜ ይደገማል፤ አንዴ ራሱ የከሳሽነት ቃል ሲሰጥ፣ ሁለቴ ምስክሮች ቃላቸውን ሲሰጡ፡፡ ቃሉ በተጠራ ቁጥር በከፊልም ቢሆን አመልካች መሸማቀቁ አይቀርለትም፡፡ ባይሸማቀቅ እንኳን ጥጋበኛውን ሰዳቢ እያስታወሰ በውስጡ ይበግናል፡፡

በምርመራ ሂደት ተጠርጣሪው እንዲቀርብ በተበዳይ በኩል መጥሪያ ይላክለታል፡፡ መጥሪያ ሲቀበል ብቻውን አይሆንም፡፡ ጓደኛቹ፣ የሥራ ባልደረቦቹ፣ ጎረቤቶቹ ይኖራሉ፡፡ የፖሊስ ጣቢያ ማህተም ያረፈበት ሰነድ ሲያዩ ስለጉዳዩ ይጠይቁታል፡፡ በድንገተኛ አጋጣሚ በተፈጠረ አለመግባባት ወይም ጥል እንደሰደበው ይነግራቸዋል፡፡ ወይም አመልካች ራሱ ቀድሞ ስለሰደበው እርሱም በተራው እንደሰደበው ይነግራቸዋል፡፡ መቼም ‘ምን ብለህ ሰደብከው?’ ብለው መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ በዚህ መልኩ የአመልካችን መሰደብ በትንሹ ተጨማሪ 3 ሰዎች ሰሙ ማለት ነው፡፡

ተጠርጣው ፖሊስ ጣቢያ ሲቀርብ በቀላሉ ወደ ቤቱ አይመለስም፡፡ ማረፊያ ቤት ይገባል፡፡ በነጋታው ወይም ከሁለት ቀናት በኋላ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ መርማሪ ፖሊስ እንደለመደው ምርመራዬን አላጠናቀቅኩም ብሎ የጊዜ ቀጠሮ ይጠይቅበታል፡፡

ተጠርጣሪው በጊዜ ቀጠሮ ሲቀርብ ‘እከሌን እንዲህ ብሎ ስለሰደበው’ ተብሎ ቁጥር በያዘ የፍርድ ቤት መዝገብ ላይ ይመዘገባል፡፡ ይህ መዝገብ እንደ ምርመራው መዝገብ ሁሉ ለብዙ ዓመታት የአመልካችን የመሰደብ ታሪክ የሚናገር መንግስታዊ ሰነድ ሆኖ ይቆያል፡፡ ተጠርጣሪው ጥፋቱን በወ/መ/ስ/ስ/ህግ ቁ. 35 መሰረት ካመነ ይህም በመዝገቡ ላይ ይሰፍራል፡፡ ዳኛው ይሰሙታል፡፡ ሬጅስትራር እና ፋይል ከፋች ምናልባትም ችሎት ጸሐፊ እየተቀባበሉ ያነቡታል፡፡ በፖሊስ ጣቢያ ቆይተው የጊዜ ቀጠሮ የሚጠባበቁ ተጠርጣሪዎችም ዜናው ይደርሳቸዋል፡፡ መቼም ‘ምን አጥፍተህ ገባህ?’ እያለ መጠየቃቸው፣ ሌሊቱን ማውጋታቸው አይቀርም፡፡ አመልካች ራሱ ‘እከሌ እንዲህ ብሎ ሰደበኝ’ ብሎ በማመልከቻው ላይ እንደወረደ ያሰፈረው ጸያፍ የስድብ ቃል በዚህ መልኩ በፍጥነት ይዛመታል፡፡

በመጨረሻም የምርመራ መዝገቡ ተጠናቆ ለዓቃቤ ህግ ሲላክ ቢያንስ 5 ዓቃቤ ህጎች (በ1 ለ5 ተጣምረው) የአመልካችን መሰደብ ያውቃሉ፡፡ ከተጠርጣሪው አፍ የወጣው ጸያፍ ቃል ሳቅ የሚያጭር ከሆነ በር ዘግተው በሳቅ ፍርስ ይላሉ፡፡ የግል ገጠመኛቸውን እያነሱ በጉደኛው መዝገብ ይዝናናሉ፡፡

በመጨረሻም በሰነድ እና በሰው በፍጥነት የተሰራጨውና (ምናልባትም የድራፍትና የቡና ማጣጫ የሆነው) ጸያፍ ቃል በዐቃቤ ህግ ክስ ላይ እንደወረደ ተጽፎ ለመደበኛ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ ክሱን ሬጅስትራርና ዳኛው ያነቡታል፡፡ ከሁሉ የከፋው ደግሞ ምስክሮች በችሎት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲናገሩት ታዳሚው ሁሉ ይሰማዋል፡፡ ለዛውም በተደጋጋሚ፡፡ በዋና ጥያቄ ተከሳሽ የግል ተበዳይን ምን እንዳለው? ዓቃቤ ህግ ይጠይቃል፣ በመስቀለኛ ጥያቄ ‘አንተ እንዲህ ስለው ሰምተሃል?’ ሲል ተከሳሽ ይጠይቃል፡፡ ዳኛውም በማጣሪያ ጥያቄ ‘ተከሳሹ የግል ተበዳይን በትክክል ምንድነው ያለው?’ ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ምስክሩ ለእያንዳንዱ ጠያቂ ምላሽ ሲሰጥ ቃሉን ከአንድ ጊዜ በላይ ይጠራዋል፡፡ ተከሳሽ ሸረኛ ከሆነ ደግሞ በመስቀለኛ ጥያቄ ሰበብ ‘እኔ ተከሳሹን እንዲህ ብየዋለው?’ ‘እሺ እንዲህ ስለው አንተ የት ነበርክ?’ ‘እንዲህ ብዬ የሰደብኩት ጮክ ብዬ ነው?’…እያለ የግል ተበዳይን በድጋሚ ሊያሳርረው ይችላል፡፡

የግራ ቀኙ ማስረጃና ክርክር ተመርመሮ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሲሰጥ የጸያፍ ቃሉ መዛመት ያበቃለታል ተብሎ ይገመታል፡፡ እውነታው ግን ከግምቱ የተለየ ነው፡፡ ጸያፍ ቃሉ በውሳኔውም ላይ ፈጦ ይታያል፡፡ ከተከሳሽ አፍ የወጣው ለጆሮ የሚዘገንን ቃል በሚዘገንን መልኩ የውሳኔው አካል ይሆናል፡፡ ለዛውም እየተደጋገመ፡፡ ከሳሽ ዓቃቤ ያቀረበው ክስ ሲገለጽ፣ የዓቃቤ ህግ ምስክሮች ቃል ሲዘገብ፣ ፍርድ ቤቱ ምክንያት ሲሰጥ፣ ድምዳሜ ላይ ሲደርስ ቃሉ በጥሬው ይደጋገማል፡፡

በግምት ከሁለት ወራት በፊት ዓቃቤ ህግ የመንግስትን ክብር አንቋሸሸ ባለው ግለሰብ ላይ ያቀረበው ለየት ያለ ክስ በማህበራዊ ድረ-ገጽ ላይ ተለቆ ነበር፡፡ ይኸው ግለሰብ መንግስትን “ቡሽቲ ነው፡፡” እንዳለና ሌሎች ቅስም ሰባሪ አስጸያፊ ቃላትን እንደተናገረ በክሱ ዝርዝር ላይ ተጠቅሷል፡፡ የክሱ መቅረብ ከተከሳሽ አፍ የወጡትን አጸያፈ ቃላት አሉታዊ ውጤት አጋነነው እንጂ አልቀነሰውም፡፡

እስካሁን የቀረበው ሀተታ ዓላማ በስድብ፣ ስም ማጥፋት፣ ዛቻ፣ አስነዋሪና አጸያፊ ቃላትና ድርጊት ክብራቸው ተነክቶ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች በደላቸውን በገሀድ እንዳያሰሙ አሊያም ፍትህ እንዳይሹ ተስፋ ማስቆጥ አይደለም፡፡ በወንጀል ጉዳይ ዝምታ መምረጥ ወንጀልን የሚያባብስ እንደመሆኑ መፍትሔ ማግኘቱ ግድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት የወንጀል ክስ አቤቱታዎች ከፖሊስ ጣቢያ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ የሚስተናገዱበት ስርዓት የተበዳዩን ግላዊ ሁኔታ ለአደባባይ በማያጋልጥ መልኩ በተለየ መንገድ መከናወን ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይም አስጸያፊና አስነዋሪ ቃላት እና ተግባራት በፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ የሚሰፍሩበትና የሚገለጹበት መንገድ ከተበዳይ አንጻር ብቻ ሳይሆን ከውሳኔ አሰጣጥ መርሆች አንጻር ትኩረት የሚያስፈልገው አነጋጋሪ ርዕስ ነው፡፡

እውነትነቱን ማረጋገጥ ባልችልም አንድ ወዳጄ እንዳጫወተኝ በድሮ ጊዜ አጸያፊ ቃላት በፍርድ ላይ በጥቅል ገላጭ መጠሪያ ነበር የሚገለጹት፡፡ ለምሳሌ በተለምዶ የሚታወቁ ክብር የሚነኩ አስጸያፊ ቃላት ‘ቅስም ሰባሪ’ በሚል ይመደባሉ፡፡ ስለሆነም ተከሳሹ ተበዳዩን እንዲህ ብሎ ስለደበው በማለት ቃሉን በመጠቀም ፈንታ ‘ቅስም ሰባሪ ስድብ ስለሰደበው’ የሚል አገላለጽ በውሳኔው ላይ ይሰፍራል፡፡ ከአባላዘር በሽታ፣ ከወሲብ እና ሐፍረተ ስጋ ጋር በተያያዘ ክብረ ነክ የሆኑ አጸያፊ ቃላት ደግሞ ‘ጋብቻ ከልክል’ በሚል ይፈረጃሉ፡፡

እነዚህ የአገላለጽ መንገዶች በእርግጥ ፍርድ ቤቶች ሲጠቀሙባቸው እንደነበረ ማረጋገጫ ባይኖርም በአሁኑ ወቅት የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ‘እያቆሸሹ’ የሚገኙት አጸያፊ ቃላት ግን ዘዴ ተፈልጎላቸው ተጠራርገው ሊወጡ ይገባል፡፡ ፍርድ በባህርዩ በተከራካሪዎች መካከል መብትና ግዴታ ከመፍጠር የዘለለ ውጤት አለው፡፡ እንዲያውም ይህን ግላዊ ሚናውን ከተወጣ በኋላ በዘላቂነት የሚቆየው መገለጫው ህዝባዊ ሰነድነቱ ነው፡፡ ፍርዱን ተማሪዎች ያነቡታል፤ መምህራን ይመረምሩታል፣ ተመራማሪዎች በጥልቀት ይተነትኑታል፡፡ ከዚያም አልፎ ፍላጎት ያለው የማህበረሰብ ክፍል ለተለያየ ምክንያት ያነበዋል፡፡

ከአስፈላጊነት አንጻር ካየነው የእነዚህ ቃላት መገለጽ በተከራካሪዎች መብትና ግዴታ ብሎም በፍርዱ ይዘት ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ከተከሳሹ አፍ የወጣው ቃል በዐቃቤ ህግ ክስ ላይ እስከተጠቀሰ ድረስ ፍርድ ቤቱ ‘ተከሳሽ ተበዳይን በዐቃቤ ህግ ክስ ላይ የሰፈረውን ቃል በመናገር እንደሰደበው’ በፍርዱ ላይ ጠቋሚ መግለጫ ከሰጠ የተከራካሪዎችን የይግባኝ መብት አያጣብብም፡፡

አጸያፊ ቃላት በመገኛኛ ብዙኃን በቀጥታ አይነገሩም፡፡ እነዚህ ተቋማት ምንም እንኳን እውነትን ሳያድበሰብሱ ለታዳሚያቸው የማቅረብ ግዴታ ቢኖርባቸውም ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ጸያፍ ቃላትን ቆርጠው ያስቀራሉ፡፡ ህዝብ ፊት የሚቀርብ የሚዲያ ውጤት የቱንም ያክል ቀዳሚ ዓላማው እውነትን ሳይጨምር ሳይቀንስ ለታዳሚው ማስተላለፍ ቢሆንም ጸያፍ ቃላት ለጆሮ ያልተገቡ፣ ሰቅጥጭ ነውራዊ ስሜት የሚፈጥሩ በመሆናቸው መቅረታቸው ግድ ነው፡፡ ይህ መሆኑ የሚዲያ ውጤቱ የተከበረ ያደርገዋል፡፡ በተጨማሪ የአገር ባለጌ የተናገረውን ሁሉ እንደወረደ መዘገብ ባለጌዎችን የማበረታታት ያክል ነው፡፡

እንደ ሚዲያ ውጤት ሁሉ ፍርድ ቤትም ውሳኔው ‘የተከበረ’ ሊሆን ይገባል፡፡

በተግባር እንደምናየው አብዛኛዎቹ ፍርድ ቤቶች ለስድብ እና መሰል ወንጀሎች ከሚሰጡት አነስተኛ ቦታ የተነሳ ብዙውን ጊዜ ሰዳቢ (ተከሳሽ) አንድም ቅጣቱ ተገድቦለት ወደ ቤቱ እያፏጨ ይሄዳል፡፡ አሊያም እዚህ ግባ በማይባል የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡ ሆኖም ለክሱ ምክንያት የሆነው ስድብና አጸያፊ ቃል እስከመጨረሻው የፍርዱ አካል ሆኖ ይቀራል፡፡ የግል ተበዳይ ላይ ያልተለጠፈበት ስድብ አሁን ፍርዱ ላይ ይለጠፋል፡፡ እና ማነው የግል ተበዳይን የበለጠ የጎዳው? የሰደበው ተከሳሽ ወይስ ለሰዳቢ ያጋለጠው የፍርድ ቤት ውሳኔ?