Tag: Federal Supreme Court Cassation Bench

‘ሁከት ይወገድልኝ’ – የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም

የአንድ ንብረት ባለይዞታ የሆነ ሰው ይዞታውን ለመንጠቅ ወይም በይዞታው ላይ ሁከት ለመፍጠር የሚፈፀምን ማንኛውንም ድርጊት እንዲቆም ወይም ንብረቱ እንዲመለስለት የሚያቀርበው የይዞታ ክስ

በፍ/ሕ/ቁ. 1149/1/ መሰረት የሁከት ይወገድልኝ ክስ መቅረብ የሚችለው አቤቱታ አቅራቢው ለክርክሩ መነሻ በሆነው ነገር በቀጥታ ወይም በጠባቂ ይዞታ ሲኖረው ነው፡፡ እንዲሁም የይዞታ ክስ የሚቀርበው ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ንብረት በወቅቱ ለመያዝ ምንም ዓይነት መብት በሌለው ሰው ላይ ስለመሆኑም የድንጋጌው መንፈስ ያስረዳል፡፡ የሁከት ይወገድልኝ አቤቱታ አቅራቢ በማስረጃ ማረጋገጥ ያለበት ንብረቱ በይዞታው ስር የነበረና የሁከት ድርጊት ፈፃሚው የኃይል ተግባር በመጠቀም ወይም በሚስጢር ንብረቱን የወሰደበት መሆኑን ነው፡፡ ሁከት ተፈጥሯል የሚባለው ባለይዞታ የሆነው ሰው በይዞታው ስር በሚገኘው ንብረት እንዳይገለገልበት ሌላ ሰው ጣልቃ ገብቶበት መሰናክል ሲፈጥርበት ወይም ረብሻ ሲፈጥርበት ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 80241 ቅጽ 15፣[1] ፍ/ህ/ቁ. 1149(1)

የሁከት ይወገድልኝ ክስ ለማቅረብ ከሳሹ ማስረዳት ያለበት ባለቤትነት ወይም የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዳለው ሳይሆን ክስ ያቀረበበት ንብረት ህጋዊ ባለይዞታ መሆኑ በሌላ አነጋገር ሁከት የተፈጠረበትን ነገር በእጁ አድርጎ በእውነት ሲያዝበት እንደነበር ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 38228 ቅጽ 9[2]

ሁከት እንዲወገድ በቀረበ ክስ ተከሳሽ የሚያነሳው የባለቤትነት ክርክር እራሱን የቻለ ባለቤትነት የመፋለም ክስ /petitory action/ በሚመለከተው ላይ አቅርቦ ከሚታይ በስተቀር ሁከት ተፈጥሯል ወይስ አልተፈጠረም ተብሎ ለሚያዘው ጭብጥ ተገቢነት የለውም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 27506 ቅጽ 6[3]

የሁከት ይወገድልኝ ክስ ሲቀርብ በፍርድ ቤት በጭብጥነት ተይዞ መፈታት የሚገባው ጉዳይ ሁከት አለ ወይንስ የለም? የሚለው ነው፡፡

የውሉ ተገቢውን የአጻጻፍ ሥርዓት ተከትሎ አለመደረግ ይዞታው በተጨበረበረ መንገድ ስለመያዙ ወይንም በማናቸውም ሕገወጥ ሁኔታ ስለመያዙና ሁከት እንዲወገድለት ክስ ያቀረበው ከሳሽ በይዞታው በእውነት ሊያዝበት እንደማይችል አያረጋግጥም፡፡ በዚህ ረገድ ውሉ ጉድለት አለበት ከተባለ በፍ/ብ/ሕ/ቁ/1808(2) ላይ እንደተመለከተው ውሉ ፈራሽ ነው እንዲባል የክስ ምክንያት ከሚሆን በስተቀር ሁከት ይወገድልኝ ተብሎ በቀረበ ክስ ላይ ሊስተናገድ የሚችል አይሆንም፡፡

ሰ/መ/ቁ 36645 ቅጽ 9[4]

በአብላጭ ድምፅ የተሰጠ

[1] አመልካች ጽናት የሆቴል ቱሪዝም ስራዎች ኃ.የተ. የግል ማህበር እና ተጠሪ አቶ ዳመነ ነጋ /5 ሰዎች/ የካቲት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

[2] አመልካች ሐጂ መሀመድ አወል ረጃ እና ተጠሪ እነ አቶ ዲኖ በሺር /2 ሰዎች/ ታህሣሥ 7 ቀን 2001 ዓ.ም.

[3] አመልካች እነ ሣሙኤል ውብሸት እና ተጠሪ ብዙነህ በላይነህ ሐምሌ 19 ቀን 1999 ዓ.ም.

[4] አመልካች ረዳት ሳጂን አያኖ አንጀል እና ተጠሪ እነ ወ/ሮ ዓሇሚቱ ህዳር 11 ቀን 2001 ዓ.ም.

Selected Cassation decisions on Women

The Federal Supreme Court, in co-operation with Network of Ethiopian Women’s Association (NEWA) has published selected Cassation decisions related to women’s rights and women litigants.

Click the link below to download the publication.

cassation on women

በፍርድ የማይዳኙ ጉዳዮች

በፍርድ የማይዳኙ ጉዳዮችን (justiciability) በተመለከተ በፍርድ ቤቶች ዘንድ ያለው አረዳድ የፅንሰ ሀሳቡን ትክክለኛ ይዘት አያንጸባርቅም፡፡ በሰ/መ/ቁ. 51790 ቅጽ 12[1] በሰፈረው የሚከተለው ማብራሪያ መሰረት በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ ማለት ከፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ውጪ የሆነ ጉዳይ ማለት ነው፡፡

ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት ያለው ስለመሆኑ የኢ.ፌ.ዲ. ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 37/1/ ድንጋጌ በግልጽ የሚያሳየው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚሁ የሕገ መንግስት ድንጋጌ መገንዘብ የሚቻለው ደግሞ ፍርድ ቤቶች አንድን ጉዳይ (አቤቱታ) ተቀብለው ውሳኔ መስጠት የሚችለት ዳኝነት የተጠየቀበት ጉዳይ በሕግ ለሌላ አካል ያልተሰጠ ጉዳይ በሚሆንበት ጊዜ እንደሆነ መሆኑን ነው፡፡ በሕግ ተለይተው በአስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲቋጩ በተባሉ ጉዳዮች ላይ መደበኛ ፍርድ ቤት የመዳኘት የስረ ነገር ስልጣን ስለሌለው በሕጉ መሰረት ለአንድ አስተዳደር አካል ቀርቦ አስተዳደራዊ ውሳኔ የተሰጠበትን ጉዳይ ወይም ለአስተዳደር መቅረብ የሚገባውን ጉዳይ ፍርድ ቤት ሊያስተናግደውም ሆነ አከራክሮ ውሳኔ ሊሰጥበት አይችልም፡፡

ይኸው አቋም ጉዳዩ በፍርድ እንደሚዳኝ ድምዳሜ ላይ በተደረሰባቸው ውሳኔዎች ላይም ተፈጻሚ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ በሰ/መ/ቁ. 80202 ቅጽ 15[2] በተሰጠ የህግ ትርጉም መሰረት ግንባታ በጊዜው አለመጠናቀቁን ወይም የገንዘብ አቅም ማነስን አሊያም በሌላ ምክንያት አስተዳደሩ በሚወስዳቸው የኪራይ (lease) ይዞታ ማቋረጥ እርምጃዎች ላይ ባለይዞታው ቅሬታ ሲያድርበት ጉዳዩን ለማየት በሕግ በግልጽ የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው ሌላ አካል እስከሌለ ድረስ ጉዳዩ በፍርድ ሊወሰን ይገባዋል፡፡

በእርግጥ በአረዳድ ረገድ የሚታየው ብዥታ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራትም ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ በአውስትራሊያ የአስተዳደር ህግ በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይን አስመልክቶ ያለው ግንዛቤ በሚከተሉት ሀሳቦች ዙሪያ ይዋልላል፡፡

  • ጉዳዩ ከፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን ውጪ ነው፡፡
  • ጉዳዩ በፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን ክልል ውስጥ ቢወድቅም ሕዝባዊ የስልጣን መገልገልን አይመለከትም፡፡
  • ፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን አለው ነገር፡፡ ግን ጉዳዩን ለመፍታት ተቋማዊ ብቃት የለውም፡፡
  • ፍርድ ቤቱ ስልጣንም ብቃትም አለው፡፡ ሆኖም ጉዳዩን በዳኝነት ለመጨረስ ህገ መንግስታዊ ተገቢነት የለውም፡፡
  • ጉዳዩ ገና ያልበሰለ ነው፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤት ጣልቃ አይገባበትም፡፡
  • ፍርድ ቤቱ ህጋዊነትን ከማጣራት አልፎ የጉዳዩን ይዘት (merit) ሳይፈትሽ በአጣሪ ዳኝነት ሊመረምር የሚችልበት በቂ ምክንያት (grounds of judicial review) የለም፡፡
  • ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለመወሰን የሚያስችል ቅቡልነት ያለው ማስረጃ ማግኘት ወይም ማስቀረብ አልቻለም፡፡[3]

ከዝርዝሮቹ መካከል በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ በሚገባ የተገለጸው በ3ኛ እና 4ኛ ላይ ነው፡፡ የዳኝነት ስልጣን ጉዳዩን ለመዳኘት ካለመቻል የሚመነጭ ባህርይ ሳይሆን በፍርድ ቤቶች ስልጣን ላይ በህግ የተቀመጠ ገደብ ነው፡፡ አንድን ጉዳይ እንዲያይ ጥያቄ የቀረበለት ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ወይም የይግባኝ ስልጣኑ ለሌላ አካል ከተሰጠ የስረ-ነገር የዳኝነት ስልጣን ያጣል፡፡ በህግ ጉዳይ ላይ ብቻ በከፊል ስልጣን አግኝቶ ከሆነም በፍሬ ነገር ረገድ የሚደርስበት ድምዳሜ የስልጣኑን ልክ ያልፋል፡፡ ወጣም ወረደ ግን የዳኝነት ስልጣን አለመኖር ራሱን ችሎ የቆመ ሀሳብ በመሆኑ ከጉዳዩ ለመዳኘት አለመቻል ጋር ሊቀላቀል አይገባውም፡፡

በዝርዝሩ 2ኛ ላይ የተጠቀሰው ‘ህዝባዊ ስልጣን’ ጉዳዩ የአስተዳደር ህግ ጥያቁ እንደማያስነሳ ያመለክታል፡፡ ሁለት የተለያየ የአስተዳር ህግ እና የፍትሐ ብሔር ስርዓት ላለቸው አገራት ይህ ነጥብ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ አቤቱታ የቀረበበት ጉዳይ መነሻው መንግስት እንደ ግለሰብ ያሉትን መብቶች ተጠቅሞ የፈጸመው ድርጊት ከሆነ በአጣሪ ዳኝነት አይስተናገድም፡፡ ከውል ውጪ ኃላፊነት ወይም ከውል በሚመነጭ ግዴታ መንግስት ተጠያቂነት ካለበት ጉዳዩ ከመነሻው የአጣሪ ዳኝነት ጥያቄ አያስነሳም፡፡

የጉዳዩ አለመብሰል እና የይዘት ጥያቄ የአስተዳደር ህግ ወሰንን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች አስተዳደሩ ገና ውሳኔ ላይ ያልደሰበትን ጉዳይ የማያዩት ህጋዊነቱን የሚመዝኑበት በቂ ምክንያት ስለማያገኙ ነው፡፡ የውሳኔው ይዘት ማለትም ትክክለኛነቱ እንዲሁ ከህግ አንጻር የሚጣራበት መሰረት የለም፡፡ በመጨረሻም ማስረጃ ሊገኝ አለመቻሉ ወይም እንዲቀርብ የታዘዘው ማስረጃ ሚስጥራዊ ተብሎ በመፈረጁ የተነሳ ፍርድ ቤቱ እልባት ለመስጠት አለመቻሉ ጉዳዩ ከመነሻው በፍርድ እንደማይዳኝ አያመለከትም፡፡

በዝርዝሮቹ 3ኛ እና 4ኛ ላይ የሰፈረውን ሀሳብ በከፊል በሚያቅፍ መልኩ በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ ማለት ምን እንደሆነ ትክክለኛ ትርጓሜ የተሰጠው በሰ/መ/ቁ. 42150 ቅጽ 12[4] ከአብላጫው ድምጽ በተለየው ሀሳብ ላይ ነው፡፡ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

አንድ ጉዳይ በፍርድ ሊያልቅ የሚችል ነው የሚባለው የክርክሩ መሠረታዊ ባህሪ በፍርድ ለመጨረስ አመች የሆነ ሲሆንና ተከራካሪዎቹ የሚከራከሩበት ጉዳይ ንድፈ ሃሳባዊ ወይም ምናባዊ የፈጠራ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ሣይሆን በነባራዊ ዕውነታና ተጨባጭ በሆነ ችግር ወይም ክስተት መሠረት ያደረገ የመብት ወይም የሃላፊነት ጥያቄ ሲሆን እንደሆነ ነው፡፡

በአብላጫው ድምጽ ላይ ግን ፅንሰ ሀሳቡ ከክስ ምክንያት ጋር ተምታቷል፡፡ በአብላጫው አስተያየት አንድ ጉዳይ በፍርድ ሊያልቅ የሚችል ነው ሊባል የሚችለው፤

…የክርክሩ መሠረት በሕግ ጥበቃ ያገኘ መብት ወይም ግዴታ ሲሆን ወይም ለመብቱ ወይም ግዴታው መሠረት የሚሆን ውል መኖሩ ሲረጋገጥ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ‘ያለመዳኘት’ ከጉዳዩ ባህርይ እንጂ ከተከራካሪ ወገኖች መብት አይመነጭም፡፡ ከባህርያቱ አንጻር ሲቃኝ አንድ ጉዳይ በፍርድ ሊዳኝ አይችልም የሚባለው አንድም ከፍርድ ቤቱ ተቋማዊ ብቃት አንጻር በፍርድ ለማለቅ አመቺ ባለመሆኑ አሊያም ከህግ መንግስታዊው የስልጣን ክፍፍል አንጻር ዳኝነት መስጠት ተገቢ ስለማይሆን ነው፡፡

ከተቋማዊ ብቃት አንጻር አንዳንድ ጉዳዮች የብዙ ወገኖች ተጻራሪና ተነጻጻሪ ጥቅም ያዘሉ (polycentric) በመሆናቸው በባህርያቸው በፍርድ ቤት ሙግት ለማለቅ አያመቹም ወይም አይመቹም፡፡ እንደ ፒተር ኬን ገለጻ፤

A polycentric issue is one which involves a large number of interlocking and interacting interests and considerations.[5]

የፍርድ ቤት የሙግት ስርዓት ተጻራሪ የጥቅም ግጭት ያለባቸውን ጉዳዮች በወጉ ለመፍታት አያመችም፡፡ ፍርድ ቤቶች የሚከተሉት ጥብቅ የሙግት ስነ ስርዓት ብሎም የሚመደብላቸው ውስን የገንዘብና የሰው ኃይል ቴክኒካልና ሳይንሳዊ መረጃና ማስረጃ ለማሰባሰብ ሆነ ተጻራሪ ጥቅሞችን በማቻቻል ዘላቂ መፍትሔ ለመቀየስ አያስችልም፡፡ በአጭር አነጋገር እነዚህን ጉዳዮች ለመዳኘት ተቋማዊ ብቃታቸው አይፈቅድላቸውም፡፡

በፍርድ ለመዳኘት ህገ መንግታዊ ተገቢነት የሌላቸው ጉዳዮች በፈራጆች ውሳኔ ሳይሆን በተመራጮችና ፖለቲከኞች ጥበብና ብልሀት ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጣቸው የፖሊሲ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ዳኞች ተሿሚዎች እንጂ ተመራጮች አይደሉም፡፡ ለመራጩ ህዝብም ቀጥተኛ ተጠያቂነት የለባቸውም፡፡ ስለሆነም አገራዊ ፋይዳ ባላቸው የፖሊሲ ጥያቄዎች ላይ ዳኝነት ለመስጠት የሚያስችል ህገ መንግስታዊ ስልጣን የላቸውም፡፡ ለምሳሌ የውጭ ጉዳይ፣ መከላከያ እንዲሁም የብሔራዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ዳኝነት መስጠት ከፍርድ ቤቶች ህገ መንግስታዊ ሚና አንጻር ተገቢነት የለውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዓለም ዓቀፍ ስምምነት መዋዋል፣ የሚኒስትሮች ሹመትና ሽረት፣ ፓርላማ የመበተን ስልጣን፣ ለህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረግ፣ መንግስት በአንድ አካባቢ መሰረት ልማት ለመዘርጋት የሚደርስበት ውሳኔ በአጠቃላይ የመንግስት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ውሳኔ ፖለቲካዊ ተገቢነት መዝኖ ፍርድ ማሳረፍ የዳኝነት አካሉ ሚና አይደለም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በዳኝነት ማየት የስልጣን ክፍፍል መርህን ይጥሳል፡፡

በውሳኔ ሰጪው ፈቃደ ስልጣን የሚወሰኑ ጉዳዮች እንዲሁ በፍርድ ለማለቅ አመቺ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ የስራ ፈቃድ ወይም የግንባታ ቦታ ጥያቄዎች ተገቢነት በፍርድ ቤት ጭብጥ ተይዞበት የሚወሰን አይደለም፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶችና ሁኔታዎች አንድ ጉዳይ በፍርድ የማይዳኘው የክሱ ምክንያት በይዘቱ ዳኝነት ለመስጠት አመቺ ሳይሆን እንዲሁም ህገ መንግስታዊ ተገቢነት ሳይኖረው ሲቀር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለክርክሩ መነሻ የሆነው አስተዳደራዊ ውሳኔ ወይም ድርጊት ‘የጀርባ ምክንያት’ ፖለቲካዊ ነክ መሆኑ ፍርድ ቤቶች አከራክረው ውሳኔ ከመስጠት አያግዳቸውም፡፡ በሰ/መ/ቁ. 48217[6] አመልካች በህጋዊ መንገድ ተመርተው የሰሩት ቤት በ1ኛ ተጠሪ ተነጥቀው ለ2ኛ ተጠሪ እንደተሰጠባቸው በመግለጽ እንዲመለስላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የቤቱ አሰጣጥ መነሻ አመልካች በጦርነት ምክንያት ቤትና ንብረት ስለወደመባቸው ለተፈናቃዮች ምትክ ቦታና ገንዘብ እንዲሰጥ መንግስት ባስተላለፈው ውሳኔ ነው፡፡ አመልካች በዚሁ መሰረት የራሳቸውን ገንዘብ ጨምረው ቤቱን ሰርተው ከጨረሱ በኋላ ‘ኤርትራዊ ነሽ’ በሚል ምክንያት 1ኛ ተጠሪ ቤታቸውን ነጥቆ ለ2ኛ ተጠሪ ሰጥቷል፡፡ ክሱ በቀረበበት ፍርድ ቤት 1ኛ ተጠሪ የቤቱ አሰጣጥ ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን በመጥቀስ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዳይዳኝ የመጀሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያነሳ ቢሆንም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ሆኖም ክርክሩን በይግባኝና በሰበር ያዩት ፍርድ ቤቶች ጉዳዩ በአስተዳደር እንጂ በፍርድ እንደማያልቅ አቋም በመያዛቸው የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሸሯል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰ/ሰ/ችሎት በበኩሉ በድርጊቱ ይዘት ላይ በማተኮር የአመልካች የክስ ‘አለአግባብ ቤቴን ተነጠቅኩኝ’ በሚል የቀረበ እንደሆነ በመጠቆም ጉዳዩ በፍርድ ሊያልቅ እንደሚችል ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡

የአገራችን ፍርድ ቤቶች በፍርድ አይዳኙም በሚል በራቸውን የሚዘጉባቸው ጉዳዮች አብዛኞቹ የተቋማዊ ብቃት ሆነ የፖሊሲ ጥያቄ አያስነሱም፡፡ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሞባቸው በሰበር ችሎት ከታረሙ አንዳንድ ውሳኔዎች ለመረዳት እንደሚቻለው በግለሰብና በመንግስት መካከል የሚነሱ አስተዳደራዊ ክርክሮችን ‘በፍርድ የማይዳኙት’ ውስጥ የመፈረጅ አዝማሚያ በፍርድ ቤቶቻችን ዘንድ ሰፍኖ ይታያል፡፡

በሰ/መ/ቁ. 75414 ቅጽ 14[7] የባለቤትነት ምስክር ወረቀት እንዲሰረዝ የቀረበ አቤቱታ ‘በፍርድ አይዳኝም’ በሚል በስር ፍርድ ቤቶች ውድቅ የተደረገ ቢሆንም የሰበር ችሎት የሚከተለውን ሐተታ በማስፈር ሽሮታል፡፡

የንብረት ባለሀብትነት መብት ከአንዱ ወገን ወደ ሌላው እንዴት መተላለፍ እንዳለበት በህጉ የተመለከተውን ደንብና ሥርዓት ሳይከተል ስለሆነ የንብረቱ ባለሀብት ስለመሆኑ የህግ ግምት መውሰጃ የሆነው የባለቤትነት ምስክር ወረቀት ቀሪ ነው፤ ሊሰረዝ ይገባል በማለት የሚቀርብ ጥያቄ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1195፣ 1196 እና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 33/2/ እና 231/1/ሀ/ በተመለከቱት ድንጋጌዎች መሠረት በፍ/ቤት ሊረጋገጥ የሚችል የዳኝነት ጥያቄ እንጂ ጉዳዩ በፍርድ ሊያልቅ የሚችል ጉዳይ አይደለም ለማለት የሚያበቃ አይደለም፡፡

በሰ/መ/ቁ. 97948 ቅጽ 17[8] የቀበሌ ቤት የተከራይነት መብት ተከራይ ሲሞት ለወራሾቹ ወይም ለቤተሰቦቹ የሚተላለፍ መሆን ያለመሆኑ በፍ/ብ/ሕጉ ስለማይንቀሳቀስ ንብረት የኪራይ ውል የተመለከቱትን ድንጋጌዎች፣ የቀበሌ ቤትን የኪራይ መብትና ግዴታ ለመግዛት በሚመለከተው አካል በወጡት ደንብና መመሪያዎች አንጻር ታይቶ በፍርድ ቤት ዳኝነት የሚሰጥበት እንጂ የቤቱ አስተዳዳሪ የሆነ ቀበሌ ለፈለገው ሰው የሚያከራየው ነው ተብሎ በፍርድ እንዳያልቅ የሚደረግ ጉዳይ እንዳልሆነ የህግ ትርጉም ተሰጥቶበታል፡፡

[1] አመልካች እነ ወልዲይ ዘሩ (61 ሰዎች) ተጠሪ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ግንቦት 16 ቀን 2003 ዓ.ም. በተጨማሪ አመልካች እነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት አስተዳደር ባለስልጣን /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ ድንቅ ስራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሰ/መ/ቁ. 54697 ቅጽ 12 መስከረም 24 ቀን 2003 ዓ.ም. ይመለከቷል፡፡

[2] አመልካች እነ አቶ ሐጎስ ሽጎዕ /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ የመሸነ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የካቲት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

[3] Chris Finn, “The concept of ‘justiciability’ in administrative law.” In Australian administrative law: Fundamentals, principles and doctrines, Matthew Groves and H. P. Lee (eds.) (Cambridge University Press, 2007) ገፅ 143-145

[4] አመልካች የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ እና ተጠሪዎች እነ አቶ ዳንኤሌ ካሣ /ሃያ ሁለት ሰዎች/ ጥቅምት 29 ቀን 2003 ዓ.ም.

[5] Peter Cane, Administrative Law, (5th edn፡ Oxford University Press, 2011) ገፅ 274

[6] አመልካች ወ/ሮ አባዲት ለምለም እና ተጠሪ እነ የዛላንበሳ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት /2 ሰዎች/ ጥቅምት 3 ቀን 2003 ዓ.ም. ቅጽ 11

[7] አመልካች ወ/ሪት ሄለን ተክሌ እና ተጠሪ ወ/ሮ ዘይድ አብርሃ ታህሳስ 21 ቀን 2007 ዓ.ም.

[8] አመልካች ወ/ሮ ዋሪቴ ሱቡሳ እና ተጠሪ እነ የጎልጆታ ከተማ አስተዳደር /2 ሰዎች/ ጥቅምት 22 ቀን 2005 ዓ.ም.

ህጋዊነትና ካርታ ማምከን

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የባለቤትነት ማረጋገጫ የመስጠት ስልጣን ያላቸው አካላት ‘ካርታ ማምከን’ የሚሉት አዲስ ፈሊጥ አምጥተዋል፡፡ ፍርድ ቤቶችም ቃሉን በተውሶ እያዘወተሩት ወደ ህግ ቃል እየቀየሩት ነው፡፡ ይህ የማምከን እርምጃ እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ በተደጋገሚ ሲስተዋል የነበረ አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ ህገ መንግስታዊ ንብረት የማፍራት መብትን አደጋ ውስጥ የከተተው ‘ከመሬት ተነስቶ’ ካርታ የማምከን ተግባር በቅርብ ሆኖ የሚቆጣጠረው በመጥፋቱ የተነሳ አስተዳደሩ ከህገ ወጥነት ወደ ጋጠ ወጥነት ተሸጋግሯል፡፡ በአስረጂነት ከሚጠቀሱ የሰበር ችሎት መዝገቦች መካከል የሰ/መ/ቁ 17712 አንደኛው ነው፡፡ በዚህ መዝገብ አመልካች ሆኖ የቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ሲሆን ተጠሪ የወሮ ሳድያ እስማኤል ወራሾች ናቸው፡፡ የጉዳዩ አመጣጥና በሰበር የተሰጠው ውሳኔ በአጭሩ እንዲህ ይተረካል፡፡

ክርክሩ የተጀመረው በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን ተጠሪዎች በውርስ የተላለፉላቸው በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁለት የንግድ ቤቶችን ተከራይተው የሚሰሩባቸው ግለሰብ ቤቶቹን እንዲያስረክቧቸውና ያልተከፈለ ኪራይም እንዲከፍሉ በማለት ክስ ያቀርባሉ፡፡ ፍርድ ቤቱም መብታቸውን በማረጋገጥ ወሰነላቸው፡፡ ከውሳኔ በኋላ የአዲስ አበባ መስተዳደር ቤቶቹ በአዋጅ ቁጥር 47/67 የተወረሱና ከዚህ ቀደም ተሰጥቶ የነበረው የባለቤትነት ደብተር በአዲስ አበባ አስተዳደር ሥራና ከተማ ልማት ቢሮ የቤቶች ጉዳይ መምሪያ የተሰረዘ መሆኑን በመግለፅ በክርክሩ ውስጥ በተቃውሞ ገብቶ የባለቤትነት ጥያቄ ያነሳል፡፡

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ እና በይግባኝ ያዩት የስር ፍ/ቤቶች ‘ቤቶቹ ስለመወረሳቸው የሚያረጋግጥ የመረካከቢያ ቅፅ አልቀረበም’ በሚል የአስተዳደሩን ጥያቄ ውድቅ አደረጉት፡፡ አስተዳደሩ የሥር ፍርድ ውሳኔዎች መሠረታዊ የሕግ ስህተት ስላለባቸው ይታረምልኝ በማለት የሰበር አቤቱታ በማቅረቡ የሰበር ችሎት የሚከተለውን ውሳኔ በድምፅ ብልጫ ሰጠ፡፡

በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1195 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ በግልፅ እንደተመለከተው የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብትነትን በማወቅ በአስተዳደር ክፍል ለአንድ ሰው የተሰጠ የባለሃብትነት የምስክር ወረቀት ማስረጃ ለተሰጠው ሰው ለዚሁ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብት እንደሆነ እንደሚያስቆጥረው ተመልክቷል፡፡ በአንፃሩ ማስረጃው የተሰጠው ከደንብ ውጭ በሆነ አሰራር መሆኑ በተረጋገጠ ጊዜ ከፍ ብሎ በፍትሐብሔር ቁጥር 1195 ላይ የተመለከተው የሕሊና ግምት ፈራሸ እንደሚሆን የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1196 (1) ይደነግጋል፡፡ በያዝነው ጉዳይ በሕግ አግባብ ስልጣን ተሰጥቶት ይህን መሰሉን የባለሃብትነት ማስረጃ የሚሰጠው ክፍል ቁጥር 5127386 የሆነው የባለሃብትነት የምስክር ወረቀት የሰረዘው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በተሰረዘ የባለሃብትነት ምስክር ወረቀት ደግሞ የሚገኝ የባለሃብትነት መብት አይኖርም፡፡ የተጠሪ ወራሾችም አውራሻቸው ያልነበራቸውን መብት ሊወርሱ አይችሉም፡፡

ለንፅፅር እንዲረዳ በሓሳብ ልዩነት የተሰጠውን አስተያየትና ምክንያት ማየቱ ተገቢ ነው፡፡

አመልካች የአዲስ አበባ መስተዳደር በቤቶቹ ላይ መብት አለኝ የሚለው በመንግስት የተወረሱ ናቸው በሚል መሆኑን መዝገቡ ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ ቤቶቹ በመንግስት የተወረሱ መሆናቸውን የሚያሳይለት ማስረጃ አላቀረበም፡፡ ለተጠሪዎች አውራሸ ተሰጥቶ የነበረው የባለቤትነት ደብተር ተሰርዟል ማለቱ ብቻውን ለእርሱ መብት የሚሰጠውና አቤቱታውም በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 358 አግባብ እንዲሰተናገድለት ለማድረግ የሚያስችል አይደለም፡፡ በኔ እምነት የሥር ፍርድ ቤቶች ወደ ዋናው ጉዳይ ተመልሰው ክርክሩን እንደገና መመርመር ሳያስፈልጋቸው አመልካቹን ወደ ክርክሩ ለመግባት የሚያስችልህ መብት መኖሩን አላስረዳህም በሚል ከወዲሁ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጋቸው የፈፀሙት የሕግ ስህተት የለም፡፡

የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1195 ግምት በፍ/ሕ/ቁ 1196 በተደነገገው መሠረት ማለትም በሕጉ መሠረት ፈራሸ ሊሆን ይችላል፡፡ የባለቤትነት ካርታው ከደንብ ውጭ የተሰጠ ከሆነ መሰረዙን ህግ ይፈቅዳል፡፡ ሆኖም የመሰረዝ ስልጣን ያለው አካል የካርታው አሰጣጥ ከደንብ ውጭ ስለመሆኑ የማስረዳት ግዴታውን ሊወጣ ይገባል፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳደር ሥራና ከተማ ልማት ቢሮ የቤቶች ጉዳይ መምሪያ ካርታውን ሲሰርዝ ካርታው ከደንብ ውጭ የተሰጠ መሆኑን የማሳየትና የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ ይህን ካላደረገ እርምጃው ከሥልጣን በላይ እንደመሆኑ በሕግ ፊት ዋጋ አይኖረውም፡፡ አመልካች ካርታው ከደንብ ውጭ ስለመሆኑ ወይም ቤቱ በአዋጅ ስለመወረሱ በክርክሩ ቢጠቅስም ከአባባል ያለፈ በተጨባጭ ማስረዳት አልቻለም፡፡ ስለሆነም የመሰረዝ ድርጊቱ የሕጋዊነት መርህን የሚጥስ፣ የሕግ የበላይነትን የሚጻረር፣ ከሥልጣን በላይ የሆነ ድርጊት ነው፡፡

የአብላጫው ድምፅ ይህን መሠረታዊ ጭብጥ አላነሳውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ካርታው በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1196 (1) መሠረት ተሰርዞ በምትኩ ለሌላ 3ኛ ወገን ሲተላለፍ ያ ሶስተኛ ወገን የቤቱ ሕጋዊ ባለቤት ስለመሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድር ባለቤትነቱ የተሰረዘውን የንግድ ቤት የራሱ ሃብት ሲያደርገው በሕጉ መሠረት የባለቤትነት መብት የተሰጠው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ በአዋጅ ቁ 47/67 ተወርሷል የሚል ከሆነ እንደተወረሰ በበቂ ማስረጃ ማሳየት አለበት፡፡ አመልካች የቤቱ ባለቤት ስለመሆኑ አሁንም በአብላጫው ድምፅ ላይ ጭብጥ ሆኖ ተነስቶ ድምዳሜ ላይ አልተደረሰበትም፡፡ በእርግጥ በተሰረዘ የባለሀብትነት የምስክር ወረቀት የሚገኝ የባለሀብትነት መብት አይኖርም፡፡ ከዚህ ድምዳሜ በፊት ግን የህግ የበላይነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡

ተጠሪዎች እየሞገቱ ያሉት የመሰረዙን ሕጋዊነት ነው፡፡ የተጠሪዎች ሙግት በአብላጫው ድምፅ ሰሚ አላገኘም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ካርታው ከደንብ ውጭ ለአመልካች እንደተሰጠ ስላላስረዳ ድርጊቱ ሕገ ወጥ ወይም ከሥልጣን በላይ ነው፡፡ በቤቱ ላይ በሕጉ መሠረት ባለቤት እንደሆነ ስላላስረዳም ‘ከመሬት ተነስቶ በሌላ ሰው መብት ባለቤትነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ይህን ሀሳብ በአነስተኛ ድምፅ አስተያየት ስንቋጨው፤

አመልካች እንኳንስ መብት ሊኖረው ቀድሞውኑ በተቃውሞ ወደ ክርክር ውስጥ እንዲገባ ሊፈቀድለት አይገባም ነበር፡፡

በሌላ ተመሳሳይ መዝገብ እንዲሁ ፍርድ ያረፈበት የባለቤትነት መብት አስተዳደሩ ስላመከነው መና ሆነ ቀርቷል፡፡ በሰ/መ/ቁ. 22719[1] ተጠሪ በሁለት የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር /ካርታ/ የተመዘገቡ ሶስት የቤት ቁጥር የተሰጣቸው ቤቶች የራሳቸው መሆናቸው ተረጋግጦ በፍርድ ቤት ውሳኔ አርፎባቸው በአፈጻጸም መዝገብ ቤቶቹን ተረክበዋል፡፡ የፍርድ ሂደቱ እንደተጠናቀቀ አመልካች የቤት ማረጋገጫ ደብተሮቹን በመሰረዙ ተጠሪ ክስ አቀረቡ፡፡ በሰበር ችሎት በነበረው ክርክር ችሎቱ ተጠሪ መብታቸውን በፍርድ ቤት አስከብረውና አረጋግጠው የተፈጸመባቸው ዓይን ያወጣ ህገ ወጥ ተግባር ከማረምና የህግ የበላይነትን ከማስከበር ይልቅ ክስ የማቅረብ መብታቸውን ነፍጓቸዋል፡፡ ችሎቱ ለማመዛን እንደሞከረው፡

አመልካች የተጠሪን የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነዶች ከሰረዘ ተጠሪ አስቀድሞ በተጠቀሱት ቤቶች ላይ ባለመብት መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን በእጁ ማስገባት ይኖርበታል፡፡ ይህ መሠረታዊ ማረጋገጫ ሰነድ ወይም ማስረጃ ሳይኖረው ፍ/ቤት ሰነድ እንዲሰጠው እንዲወሰንለት መጠየቅ አይቻልም፡፡

በአጭር አነጋገር ቤቱን በአስተዳደሩ ህገ ወጥ ተግባር የተነጠቀ ሰው ቤቱ እንዲመለስለት የመጠየቅ መብት እንኳን የለውም፡፡

የሰበር ችሎት ዘግይቶም ቢሆን የሰ/መ/ቁ 17712 እና 22719 ውሳኔ ካገኙ ከሰባትና አምስት ዓመታት በኋላ ፍጹማዊ በሆነውና ፍጹማዊነቱንም ችሎቱ ይሁንታ በሰጠው የአስተዳደሩ ካርታ የማምከን ስልጣን ላይ ገደብ ለማበጀት ተገዷል፡፡ በሰ/መ/ቁ. 42501[2] ፍርድ ባረፈበት ጉዳይ ካርታ ማምከን ህገ ወጥነቱን ጠንከር ባሉ ቃላት እንደሚከተለው ገስጾታል፡፡

አንድ የአስተዳደር አካል በፍርድ ቤት ክርክር መረታቱን ከተረዳ በኃላ በሕጉ የተሰጠውን ስልጣን መነሻ በማድረግ ለፍርዱ መሰጠት መሠረት የሆነውን ማስረጃ ዋጋ በማሣጣቱ ምክንያት የፍርድ አፈፃፀም ዋጋ እንዲያጣ የማድረግ ውጤት በኢ.ፊ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 78/1/ እና 79/1/ እና /4/ ስር የተረጋገጠውንና የተከበረውን የነፃ ፍርድ ቤት መኖርንና የዳኝነት ስልጣን ትርጉም አልባ የሚያደርገው ነው፡፡

[1] አመልካች የአ/አ/ ከተማ አስተዳደር ስራ ከተማ ልማት ቢሮ ተተኪ የመሬት ልማትና አስተዳደር ባለስልጣን እና ተጠሪ አቶ ነጋሽ ዱባለ ጥር 14 ቀን 2000 ዓ.ም. ቅጽ 6

[2] አመልካች የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ እና ተጠሪ የአስር አለቃ ደምሴ ዳምጤ ወራሾች /3 ሰዎች/ የካቲት 28 ቀን 2005 ዓ.ም.

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የአጣሪ ዳኝነት (judicial review) ስልጣን

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ስልጣን በቀጥታ ከህገ መንግስቱ ይመነጫል፡፡ ሆኖም የስልጣኑን ወሰን የሚያሰምረው የህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ ሀ የአማርኛውና እንግሊዝኛው ቅጂ ግልጽ መፋለስ ይታይበታል፡፡ በአማርኛው ንባብ የሰበር ችሎት መሰረታዊ ‘የህግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ’ የማረም ስልጣን ይኖረዋል፡፡ (ሰረዝ የተጨመረ) የእንግሊዝኛው ቅጂ ደግሞ over any final court decision የሚል አገላላጽ በመጠቀም ስልጣኑን ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ በሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ይገድበዋል፡፡

የድንጋጌውን ይዘት ዝርዝር የሚወስነው ህግ ከእንግሊዝኛው ቅጂ ጋር ይስማማል፡፡ በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁ. 25/1988 አንቀጽ 10 የፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሰበር ስልጣን የሚያገኝባቸው ሶስት ጉዳዮች ተዘርዝረዋል፡፡ እነዚህም፤

  • የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች
  • የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች
  • የክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት መደበኛ ችሎት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች

በሶስቱም ጉዳዮች በውሳኔ ሰጭነት የተጠቀሱት ተቋማት መደበኛ ፍርድ ቤቶች ብቻ ናቸው፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ረ ህገ መንግስት አንቀጽ 80/3/ ሀ የእንግሊዝኛው ቅጂ ላይ court የሚለው ቃል እንዲሁ ይህንኑ ሀሳብ ያንጸባርቃል፡፡ ሆኖም የአማርኛው ንባብ ውሳኔ ሰጭውን በዝምታ አልፎታል፡፡ ላይ ላዩን ሲታይ ዝምታው ለህገ መንግስታዊ ትርጉም በር የከፈተ አይመስልም፡፡ ‘የመጨረሻ ውሳኔ’ የሚለው አገላለጽ ፍርድ ቤትን ታሳቢ አድርጓል ቢባል ብዙዎችን ያስማማል፡፡

ሆኖም ችግሩ ከቋንቋ አጠቃቀም ያልዘለለ የሚመስለው የአንቀጽ 80/3/ ሀ ድንጋጌ በተግባር ህገ መንግስታዊ ጥያቄ አስነስቶ የሰበር ችሎትን የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን አስፍቶታል፡፡ በሰ/መ/ቁ. 43511[1] ከአዋጅ ውጪ የተወረሱ ንብረቶችን በተመለከተ ከፊል ዳኝነታዊ ስልጣን የተሰጠው የፕራይቬይታይዜሽን ኤጀንሲ ቦርድ ያስተላለፈው ውሳኔ በቀጥታ በሰበር እንዲታይ አቤቱታ ቢቀርብም አጣሪ ችሎቱ ጉዳዩ አስተዳደራዊ መሆኑን በመጠቆም ውድቅ አድርጎታል፡፡ ሆኖም በመዝገቡ ላይ አመልካች ሆነው የቀረቡት አቤቱታ አቅራቢዎች የውሳኔውን ህገ መንግስታዊነት በመሞገት ለህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ አቤቱታ አስገቡ፡፡ አጣሪውም ለጥያቄያቸው አዎንታዊ ምላሽ ባለመስጠቱ የመጨረሻ አማራጫቸውን በመጠቀም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አመለከቱ፡፡ ም/ቤቱ የችሎቱን ስልጣን በማረጋገጥ መዝገቡን ወደ ሰበር ችሎት መለሰው፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የቦርዱን ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የማረም ስልጣን እንዳለው በማረጋገጥ የተሰጠው ይህ የም/ቤቱ ውሳኔ ‘የመጨረሻ ውሳኔ’ በሚል በህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ ሀ ላይ የተቀመጠውን አገላለጽ ከእንግሊዝኛ ቅጂ ፍጹም የተለየ ይዘትና መልዕክት ሰጥቶታል፡፡ በውጤቱም ከፍርድ ቤት ውጭ ያሉ ከፊል የዳኝነት አካላት ላይ የሰበር ችሎት የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን እንዳለው አረጋግጧል፡፡

የም/ቤቱ ውሳኔ ህገ መንግስታዊ ፋይዳው ስር ነቀልና መሰረታዊ ነው፡፡ የስር ፍ/ቤቶችን የህግ ስህተት በማረም ብቻ ተወስኖ የነበረው የሰበር ችሎት በም/ቤቱ ‘በተጨመረለት’ ስልጣን ከፊል ዳኝነታዊ ስልጣን የተሰጣቸው የአስተዳደር አካለት የሚያስተላልፉትን ውሳኔ ጭምር የማረም የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን ይኖረዋል፡፡ ችሎቱም ዳኝነታዊ የአስተዳደር ውሳኔዎችን ማረም ህገ መንግስታዊ ሚናው እንደሆነ በሌሎች ሁለት መዝገቦች በሰጣቸው ውሳኔዎች በተግባር አረጋግጧል፡፡

በሰ/መ/ቁ. 92546[2] የድሮው ፍትሕ ሚኒስቴር የአሁኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የዲሲፕሊን ውሳኔ በቀጥታ ለሰበር ችሎት ቀርቦ ተሸሯል፡፡ አቤቱታ አቅራቢው በሚኒስትሩ የዲሲፕሊን እርምጃ የተወሰደበት ዓቃቤ ህግ ሲሆን ጉዳዩ በሰበር ችሎት ከመስተናገዱ በፊት በሌላ ፍርድ ቤት አልታየም፡፡ በመዝገቡ ላይ በችሎት የዳኝነት ስልጣን አከራካሪ ጭብጥ ሆኖ ባይወጣም የህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ ሀ እና አዋጅ ቁ፣ 25/88 አንቀጽ 10 ተጠቅሶ የቀረበውን አቤቱታ ችሎቱ መቀበሉ ሲታይ የአጣሪ ዳኝነት ስልጣኑ ጠንካራ መሰረት እየያዘ እንደመጣ እንደሆነ አስረጂ ነው፡፡ በሰ/መ/ቁ. 61221 ቅጽ 14[3] የተያዘው አቋም ይህንን ሀሳብ ያጠናክራል፡፡ በዚህ መዝገብ በሰፈረው ህግ ትርጉም በፍርድ ቤት እንዳይታዩ በመጨረሻ ማሰሪያ አንቀጽ (finality clause) ገደብ የተደረገባቸው ውሳኔዎች ሳይቀር በችሎቱ የአጣሪ ዳኝነት ስር እንዲወድቁ ተደርገዋል፡፡ ጉዳዩ የታየው አዋጅ ቁ. 714/2003 እና 715/2003 ከመውጣታቸው በፊት ሲሆን ቀድሞ በነበሩት የጡረታ ህጎች የማህበራዊ ዋስትና ጉባኤ ውሳኔ የመጨረሻ በመሆኑ በይግባኝ ሆነ በቀጥታ ክስ በመደበኛ ፍ/ቤቶች ሊታይ አይችልም፡፡

በሰ/መ/ቁ. 61221 የሰበር አቤቱታ የቀረበው የጉባዔውን የመጨረሻ ውሳኔ በመቃወም ነው፡፡ ሆኖም በችሎቱ የዳኝነት ስልጣን ላይ በተጠሪ በኩል ተቃውሞ በመቅረቡ የስልጣን ምንጭ አከራካሪ ጭብጥ ሆኖ ወጥቷል፡፡ ይህንን በማስመልከት ህገ መንግስቱን እና አዋጅ ቁ. 25/88 በማጣቀስ የሚከተለው የህግ ትርጉም ተሰጥቷል፡፡

ጉዳዩ በተነሳበት ጊዜ ስራ ላይ በነበረው ሕግ አግባብ ማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው ከተባለ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 በተመለከተው አግባብ ለዚህ ሰበር ችሎት አቤቱታ ከማቅረብ የሚከለክል ሕጋዊ አግባብ የለም፡፡

 

[1] አመልካች የሟች አቶ ዋሲሁን መኮንን ሚስትና ወራሾች /8 ሰዎች/ እና ተጠሪ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ሰ/መ/ቁ. 43522 ቅጽ 14 ጥቅምት 23 ቀን 2005 ዓ.ም.

[2] አመልካች አቶ አብዱራዛቅ ኢብራሒም እና ተጠሪ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሰ/መ/ቁ. 92546 ቅጽ 15 ታህሳስ 18 ቀን 2006 ዓ.ም.

[3] አመልካች አቶ አከለ ምህረቱ እና ተጠሪ ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ መስከረም 22 ቀን 2005 ዓ.ም.