Tag: Ethiopian criminal procedure

የእምነት ቃል —የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም

በወንጀል ተጠርጣሪ ግለሰብ በምርመራ ሂደት ወይም ደግሞ ተከሳሽ በክሱ ሂደት የራሱን አጥፊነት በመቀበል የሚሰጠው ቃል

አንድ ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ በምርመራ ሂደትም ሆነ ክስ ከቀረበበት በኃላ ክሱን ለሚሰማው ፍርድ ቤት የሚሰጠው የእምነት ቃል በሕግ ተቀባይነት ካላቸው የማስረጃ ዓይነቶች ውስጥ የሚካተት መሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 27፣ 35 እና 134 ድንጋጌዎች ተመልክቷል፡፡ ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ የዚህ ዓይነቱን የእምነት ቃል የሚሰጠው የራሱን አጥፊነት አምኖ በመቀበል እንደሆነ የሚገመት በመሆኑ ሌሎች ተጠርጣሪዎች፣ ተከሳሾች ወይም ማናቸውም ሌላ ሰው በወንጀሉ አደራረግ ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው ስለመሆኑ ወይም ስላለመሆኑ በእምነት ቃሉ ውስጥ የሚገልጻቸው ፍሬ ነገሮች ምናልባት ለቀጣይ ምርመራ ፍንጭ ሊሰጡ ይችሉ ይሆናል ከሚባል በቀር በማናቸውም ሰው ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ሕጋዊ ውጤት ሊያስከትሉ የሚችሉ ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉበት የሕግ አግባብ የለም፡፡

በሌላ አነጋገር አንድ ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ በምርመራ ሂደትም ሆነ ክሱን ለሚሰማው ፍርድ ቤት የሚሰጠው የእምነት ቃል ውጤት በራሱ በቃል ሰጪው ላይ ተወስኖ የሚቀር ከመሆኑ ውጪ ወደሌሎች ተጠርጣሪዎች ወይም ተከሳሾች ሊተላለፍ የሚችል አለመሆኑን ከላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች አነጋገር እና ይዘት መገንዘብ የሚቻል ከመሆኑም በላይ ወንጀሉን የፈጸሙት በጋራ ወይም በመተባበር መሆኑን በማመን አንደኛው ተከሳሽ የሚሰጠው የእምነት ቃል ወንጀሉን አልፈጸምኩም በማለት ክዶ በሚከራከረው ሌላኛው ተከሳሽ ላይ ሕጋዊ ውጤት ሊያስከትል የማይችል ስለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 94450 በ25/07/2006 ዓ.ም. የሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በተያዘው ጉዳይ ላይ ተፈጻሚነት ያለው መሆኑን ተገንዝበናል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 96310 ቅጽ 17፣[1] ወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 27፣35 እና 134

በወንጀል ጉዳይ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 134(1) እንደተደነገገው ተከሣሹ የተከሰበበትን የወንጀል ክስ ይዘት በሚገባ ተረድቶ አድራጐቱን እንደቀረበበት የወንጀል ክስ ዝርዝር መፈፀሙን አምኖ የእምነት ቃል በሰጠ ጊዜ ይህ የእምነት ቃል ለቀረበበት የወንጀል ክስ ማስረጃ ሆኖ በዚሁ ማስረጃ መሠረት የጥፋተኝነት ውሣኔ መስጠት የሚቻልበት ሥርዓት ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ አኳኋን ተከሣሹ የሚሰጠው የእምነት ቃል በማስረጃነቱ ተይዞ የሚሰጠው የጥፋተኛነት ውሣኔ ውሣኔውን በሰጠው ፍ/ቤቱ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም፡፡ በዚህ ውሣኔ ቅሬታ የተሰማው ወገን በህገ-መንግስቱም አንቀጽ 20(6) ሆነ በዝርዝር በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ሕጉ መሠረት ከታች ወደ ላይ በይግባኝ የመከራከር መብቱን ለማስጠበቅ የይግባኝ አቤቱታ የሚያቀርብበት ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡

በዚህ መሠረት በይግባኝ በሚቀርበው መከራከሪያ ነጥብነቱ እንደ ወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 134(1) ድንጋጌ አነጋገር የወንጀሉን አድራጐት ለመፈፀሙ የእምነት ቃል አልሰጠሁም፤ ነገር ግን እንዳመንኩ ተደርጎ ጥፋተኛ ነህ ተብያለሁ በማለት ቅሬታ የቀረበ እንደሆነ ተከሳሹ ተላልፎታል በሚል የተጠቀሠበት ድንጋጌ ሥር የተቋቋመውን የወንጀል ዝርዝር ተከሣሹ በአፈፃፀሙ ረገድ የሰጠውን ዝርዝር የአፈፃፀም ሁኔታ በማገናዘብ በእርግጥም እንደ ክሱ የወንጀሉን አድራጐት ፈጽሞታል ወይስ አልፈፀመውም የሚለውን ለመለየት ተከሣሹ ሰጠ የተባለው ዝርዝር የእምነት ቃል በመዝገቡ ላይ ሠፍሮ ካልተገኘ በቀር የበላይ ፍ/ቤቶች ተገቢውን ዳኝነት ለመስጠት አያስችላቸውም፡፡

ሰ/መ/ቁ 77842 ቅጽ 14፣[2] ወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 134/2/

በወንጀል የተከሰሰ ሰው ጥፋተኛ ተብሎ የሚቀጣው በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 134(1) መሠረት በሰጠው የእምነት ቃል መሰረት ከሆነ ፍርድ ቤቶች ተከሳሹ ከሰጠው የእምነት ቃል ውስጥ ተከሳሹን የሚጠቅመውን ክፍል በመተው፤ በዕምነት ቃሉ ያላስመዘገበውን ፍሬ ነገር መሰረት በማድረግ ቅጣት ሊያከብዱ አይገባም፡፡

ሰ/መ/ቁ 96954 ቅጽ 16[3]

[1] አመልካች አቶ ጉዲና ለማ ገዛኸኝ እና ተጠሪ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግስት የስ/ፀ/ሙስና ኮሚሽን ዐ/ሕግ ህዳር 26 ቀን 2007 ዓ.ም.

[2] አመልካች አቶ ሳሚ ሁሴን እና ተጠሪ የፌደራል ዐቃቤ ህግ ታህሣስ 03 ቀን 2005 ዓ.ም.

[3] አመልካች ዘፈሩ ወልደ ትንሣኤ አብርሃ እና ተጠሪ የፌዴራል ዐቃቤ ህግ ሚያዚያ 24 ቀን 2006 ዓ.ም.

“የድርጅት በቁም መክሰም!”—ሰ/መ/ቁ 100079

የሰ/መ/ቁ 100079 “ን” አንብበን ስናበቃ ለተፈጥሮ ሰው ብቻ የምንጠቀምባቸው የተለመዱ አባባሎች ለህግ ሰውም ሊውሉ የመቻላቸው አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል እንረዳለን፡፡ በውሳኔው ላይ እንደተመለከተው አንድ የህግ ሰውነት ያለው ድርጅት በህጉ አግባብ ሳይፈርስና ህልውናውን ሳያጣ “በቁሙ ሊከስም” ይችላል፡፡ የዚህ አባባል ምንጩ በውሳኔው ላይ ባይገለጽም “በቁም መሞት” ከሚለው ሰውኛ አባባል እንደተቀዳ ያስታውቃል፡፡ አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ሰው ጊዜ ይጥለውና ከሰውነት ተራ ወጥቶ በቁሙ ይሞታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ድርጅትም ማን እንደሚጥለው ባይታወቅም “ከህጋዊ ሰውነት ተራ ወጥቶ” በቁሙ ይከስማል፡፡ ድርጅት እንዲህ ሰውኛ ባህርይ የሚጋራ ከሆነ መሰል ሰውኛ አባባሎች ለድርጅት የሚውሉበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ለምሳሌ…ለሕጋዊ ሰውነት መድሀኒቱ ሕጋዊ ሰውነት ነው! ለድርጅት መክሰም አነሰው! ሕጋዊ ሰውነትን ማመን ቀብሮ ነው እና የመሳሰሉት የሕጋዊ ሰውነት አባባሎች ሆነው በቅርቡ ዕውቅና ማግኘታቸው አይቀርም፡፡

በሰ/መ/ቁ 10009 ህጋዊ ሰውነቱን ሳያጣ “በቁሙ የከሰመው” ድርጅት ሜጋ የኪነ ጥበብ ማዕከል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር ሲሆን ከመክሰሙ በተጨማሪ ሰውኛ ገጽታው በመጥሪያ አደራረስም ተንጸባርቋል፡፡ ክሱ በቀረበበት ፍ/ቤት ድርጅቱ 1ኛ ተከሳሽ የነበረ ሲሆን ክሱ በሚሰማበት ወቅት የወንጀሉ ክስና መጥሪያ አልደረሰውም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በሰበር ውሳኔው ላይ እንደተመለከተው ከሳሽ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን “የወንጀል ክሱንና መጥሪያውን ለማድረስ ጥረት አድርጎ ሊያገኘው ባለመቻሉ” ምክንያት ነው፡፡ ምናልባት መጥሪያ እንዳይደርሰው “ሆነ ብሎ እየተሸሸገ” ይሆን?

ገራሚውና አስገራሚው ነገር ድርጅቱ በቁሙ መክሰሙ አሊያም መጥሪያ እንዳይደርሰው መሰወሩ አይደለም፡፡ በሰበር ውሳኔው ላይ የሰፈረው የክርክሩ ሂደት እንደሚያሳየው ድርጅቱ በጋዜጣ አልተጠራም፡፡ ጉዳዩ በሌለበት እንዲታይም ትዕዛዝ አልተሰጠም፡፡ ሆኖም ግን በስር 2ኛ ተሳሳሽ (በሰበር መዝገቡ ላይ አመልካች) ከነበሩት የድርጅቱ የቀድሞ ስራ አስኪያጅ ጋር ጥፋተኛ ተብሏል፡፡ አመልካች ለሰበር ችሎት ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ድርጅቱ በህጉ አግባብ ተጠርቶ ቀርቦ ሳይከራከር እንዲሁም በጋዜጣ ተጠርቶ ጉዳዩ በሌለበት እንዲታይ ትዕዛዝ ሳይሰጥና በዚሁ መሰረት ጥፋተኛ ሳይባል አመልካች ጥፋተኛ ሊባሉ እንደማይገባ በመግለጽ አጥብቀው ተከራክረዋል፡፡ ሆኖም የሰበር ችሎት በስር ፍ/ቤት ውሳኔ ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ሐተታ በመጥቀስ ድርጅቱ ጥፋተኛ እንደተባለ በደረሰበት ድምዳሜ መሰረት ክርክሩን ውድቅ አድርጎታል፡፡ ድርጅቱ ጥፋተኛ የተባለበት የስር ፍ/ቤት የውሳኔ ክፍል እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

ስለሆነም ተከሳሹ የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ የሚያስተባብል ማስረጃ ያላቀረቡ በመሆኑ በ1997ዓ.ም 1ኛ ተከሳሽ ባከናወነው የንግድ እቅስቃሴ ገቢን አሳውቆ ባለመክፈልና ተከሳሾች አሳሳች መረጃ በመስጠትና ኪሳራ ሪፖርት በማድረግና ከ1996ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ የተሰበሰበውን የተጨማሪ እሴት ታክስ የሰበሰቡትን በሙሉ ሪፖርት ባለማድረጋቸው ሁለተኛው ተከሳሽ (አመልካች) በስራ አስኪያጅነታቸው አንደኛ ተከሳሽ ለፈጸመው ድርጊት ተጠያቂ በመሆናቸው ተከሳሾች በአዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 96 እና አንቀጽ 97 ንዑስ አንቀጽ 3 (ሀ) አንደዚሁም በአዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 49 ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ጥፋተኛ ናቸው’’

በእርግጥ ጥፋተኛ የሚል ቃል በውሳኔው ላይ የተጠቀሰ ቢሆንም ድርጅቱ ቀርቦ ሳይከራከር ብሎም ጉዳዩ በሌለበት እንዲታይ ትዕዛዝ ሳይሰጥ ውጤት ያለው የጥፋተኝነት ውሳኔ ሊሰጥ አይችልም፡፡ ምክንያቱም….በአጭሩ አያስኬድም፡፡ የጥፋተኝነት ውሳኔው ጸንቶ የሚቆምበት የህግ መሰረት የለውም፡፡ ከድርጅቱ ጥፋተኝነት ጋር ተያያዞ የተነሳውን ጭብጥ የበለጠ አስገራሚ የሚያደርገው ሌላም ነገር አለ፡፡ አመልካች ድርጅቱ ጥፋተኛ አይደለም በማለት በሰበር ችሎት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ የነበረው ለድርጅቱ በመቆርቆር አይደለም፡፡ የድርጅቱ ጥፋተኝነት ጭብጥ ሆኖ የተነሳው ድርጅቱ ጥፋተኛ ባልተባለበት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ (አመልካች) ጥፋተኛ ልባል አይገባም በማለት ክርክር በማቅረባቸው ነው፡፡ ይህ ጭብጥ ሊፈታ የሚችለው አንድም ድርጅቱ ጥፋተኛ ባይባልም አመልካች እንደ ስራ አስኪያጅነታቸው ጥፋተኛ የሚባሉበት የህግ አግባብ እንዳለ አቋም በመያዝ አሊያም በህጉ አግባብ በድርጅቱ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጥቷል ሊባል እንደማይገባ/እንደሚገባ ጭብጥ መስርቶ ለዚሁ ጭብጥ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው አመልካች ስለድርጅቱ ጥፋተኝነት አያገባቸውም፤ ስለ ድርጅቱ ለመከራከርም ውክልና የላቸውም የሚባል ከሆነ ግን ከመሰረታዊው ጭብጥ መራቅ ነው የሚሆነው፡፡ ይህን አስመልክቶ የችሎቱ ሐተታ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

“አመልካች ከ2003ዓ.ም ጀምሮ የአንደኛ ተከሳሽ ስራ አስኪያጅ እንዳልሆነና አንደኛ ተከሳሽንም ወክሎ ክርክር ለማቅረብ እንደማይችል በስር ፍርድ ቤት የገለጸ መሆኑን ግራ ቀኙ ካቀረቡት ክርክር ተገንዝበናል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ የወንጀል ጉዳይ የታየው የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዐት ሕግ አንቀጽ 162 አንቀጽ 167 እና ሌሎች ድንጋጌዎች ከሚደነግጉት ውጭ ነው ብሎ ካለ የስር ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ በሌለበት አይቶ የሰጠው ፍርድ እንዲነሳለት ከሚያመለክት በስተቀር አንደኛ ተከሳሽ በሌለበት ታይቶ መወሰኑን አመልካች መከራከሪያ አድርጎ ሊያቀርብ የሚችል አይደለም፡፡ አንደኛ ተከሳሽ በመወከልም አንደኛ ተከሳሽ በሌለበት ታይቶ የተሰጠው ፍርድ እንዲነሳ ለመከራከር የሚያስችለው ውክልና ወይም ስልጣን የለውም ስልጣንም ቢኖረው ክርክሩ መቅረብ የሚገባው በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ሕግ ከአንቀጽ 197 እስከ አንቀጽ 102 የተደነገጉትን ድንጋጌዎች መሰረት በማድረግ መሆን የሚገባው በመሆኑ አመልካች ያቀረበው ክርክር የሕግ መሰረት ያለው ሆኖ አላገኘነውም፡፡”

የሰ/መ/ቁ 100079 ከላይ በቅንጭቡ ከቀረበው በላይ በርካታ ዘርፈ ብዙ የህግ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡ አንባቢ በራሱ ይመዝነው ዘንድ የፍርዱ ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ ከዚያ በፊት ግን በተለየው ሓሳብ ላይ የሰፈረው የሚከተለው ቁም ነገር እንደ መንደርደሪያ ይሁን፡፡

ሕግና ሥርዓት ባለበት አገር አንደኛ ተከሳሽ የነበረው ድርጅት በእርግጥ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ህያው ድርጅት ከሆነ ከሚመለከታቸው አካላት በማጣራት እውነት የማፈላላግ ሥራ መከናወን ነበረበት፡፡ በሌላ በኩል ድርጅቱ ሜጋ ማስታወቂያ ከተባለው ድርጅት ከተዋሃዳ የተቀለቀለ / Amalgamation merge /ስለመሆኑ በክርክር ሂደት ተነስቷል፡፡ ይህ በተመለከተም ሁለቱም ድርጅቶች ተዋህደው ከሆነ መቼ እና በማን ውሳኔ ሰጪነት ተዋሀዱ የሚለው መጣራት ነበረበት፡፡

የአንድ ድርጅት ሥራአስኪያጅ ኃላፊ የሚሆነው ድርጅቱ በሕግ አግባብ ጥፋተኝነቱ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ …ድርጁቱ በህግ አግባብ መጥሪያ የደረሰው ስለመሆኑ አልተረጋገጠም፡፡ የአሁኑ አመልካችም ድርጅቱ ከለቀቁ ከአንድ ዓመት በኃላ ክስ የተመሰረተባቸው ስለመሆኑ እየተከራከሩ ነው፡፡ የስር ፍርድ ቤቶች የአሁኑ አመልካች ጥፋተኛ ከተባሉ ድርጅቱም ጥፋተኛ ነው በሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸው ከውሳኔያቸው ይዘት መረዳት ይቻላል፡፡ ይሁንና የስር ፍርድ ቤቶች ድምዳሜ የህግ መሰረት ያለው አይደለም፡፡……..ቅድሚያ መረጋገጥ ያለበት የድርጅት ጥፋት መኖር ያለመኖር ነው፡፡ አንድ ድርጅት ጥፋተኛ ነው ወይስ አይደለም ወደ ሚለው ድምዳሜ ለመድረስም በህጉ የተዘረጋው የሙግት አመራር ሥርዓት በጥብቅ [ተግባራዊ] መደረግ ነበረበት፡፡ የስር ፍርድ ቤቶች አንደኛ ተከሳሽ የነበረው ድርጅት ሕጋዊ ሰውነት ያለውና ያልከሰመ መሆን ያለመሆኑን በአግባቡ ሳያጣሩ ጥሪ ቢደረግለትም አይቀርብም በሚል ሰበብ እውነት [የማፈላለግ] ግዴታቸው (truth finding) ወደ ጎን በመተው [ሕጉ] [የዘረጋውን] የሙግት አመራር ሥርዓት ሳይከተሉ ከውሳኔ ላይ መድረሳቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት መፈጸማቸውን የሚያሳይ ነው፡፡”

የሰ/መ/ቁ 100079

መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ/ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

ሡልጣን አባተማም

ሙስጠፋ አህመድ

ተኽሊት ይመሰል

 

አመልካች፡- አቶ ዕቁባይ በርሀ ገ/እግዚአብሔር – ጠበቃ ደሳለኝ መስፍን ቀረቡ

ተጠሪ፡- የኢትዮጵያ ገቢዎች ጉምሩክ ባለሥልጣን – ዐ/ህግ ወንድዬ ብርሃኑ ቀረቡ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል

ፍ ር ድ

ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 176025 ታህሳስ 19/2005 ዓ/ም የሰጠው ፍርድና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመዝገብ ቁጥር 131320 ጥር 21 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ፍርድ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታርምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው ጉዳዩ ተጠሪ አመልካች የአንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ሲሰራ ለግብር ስብሳበው መሥሪያ ቤት አሳሳች ማስረጃ የማቅረብና ተጨማሪ እሴት ታክስ የማሳወቅና የመክፈል ኃላፊነቱን ባለመወጠት ወንጀል ፈፅሟል በማለት ያቀረበውን ክስና ክርክር የሚመለከት ነው፡፡ በሥር ፍርድ ቤት ተጠሪ ከሳሽ አመልካች ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል፡፡ Continue reading ““የድርጅት በቁም መክሰም!”—ሰ/መ/ቁ 100079”