Tag: bill of lading

ዕቃዎችን በመርከብ ስለማጓጓዝና የቻርተርፓርቲ ስምምነት (ሰ/መ/ቁ. 21776 -ያልታተመ -3 ለ 2 አብላጫ ድምፅ የተወሰነ)

                                                          የሰ/መ/ቁ. 21776

መጋቢት 17 ቀን 2001 ዓ.ም

ዳኞች፡- ዓብዱልቃድር መሐመድ

       ታፈሰ ይርጋ

       ፀጋዬ አስማማው

       አልማው ወሌ

       ዓሊ መሐመድ

አመልቾች፡- 1. ኢኬንስለር ዲስ ቲካሬት ኤ.ኤ.ስ አልቀረቡም

2.  ቱሬ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር አልቀረቡም

ተጠሪ፡- ጉና የንግድ ስራዎች ድርጅት ኃ/የተ/የግል ማህበር ጠበቃ አቶ ይስሐቅ ተስፋዬ

      መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ነበር፡፡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥሰናል፡፡

ፍ ር ድ

      ጉዳዩ የቀረበው አመልካቾች ጥቅምት 15 ቀን 1998 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር ማመልከቻ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 16/75 ሐምሌ 29 ቀን 1997 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ስላመለከቱ ነው፡፡

ክርክሩ በመጀመሪያ የታየው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በከፍተኛው ፍ/ቤት ተጠሪ በከሳሽነት ቀርቦ ከአንደኛው አመልካች አንድ ሺ ሜትሪክ ቶን፣(1000 ሜትሪክ ቶን) ብረት የገዛ መሆኑንና በቻርተርፓርቲ እቃውን ለመላክ ሌተር ኦፍ ክሬዲት አሻሽዬ እንድከፈት ጠይቆኝ በዚሁ መሰረት “ሌተር ኦፍ ክሬዲቱን” ካሻሻልኩ በኋላ አንደኛ ተከሳሽ(አመልካች) “ኤም.ቪ.ማርዋ” ከተባለ መርከብ አዛዥ ወይም የመርከብ ባለሐብት ጋር እቃውን በቻርተርፓርቲ ለማጓጓዠ ያደረገው ውል ሣይኖር እንደ አውሮፖ አቆጣጠር ግንቦት 29 ቀን 1998 ዓ.ም የቻርተርፓርቲ ውል የተዋዋለ በማስመሰል የቻርተርፓርቲ ቢል ኦፍሊዲንግ ለባንክ በማቅረብ የእቃውንና የማስጫኛውን ዋጋ ወስዷል፡፡ ስለሆነም እቃውን ጭኛለሁ ብሎ ገንዘብ የወሰደ ቢሆንም እቃውን ጫነች የተባለችው መርከብ ክሱን እስካቀረብንበት ጊዜ ድረስ የትእንዳለች ለማወቅ አልተቻለም፡፡ አንደኛ ተከሳሽ እቃውን ለመከታተልና ከአጓዡን ከመርከቡ ባለሐብት ጋር ያደረገውን ቻርተርፓርቲ ውል እንዲልክልን በተደጋጋሚ የጠይቀነው ቢሆንም ግንቦት 14 ቀን 1998 ዓ.ም በቴሌክስ በፃፈው ደብዳቤ ከመርከቡ ባሐብት ወይም ወኪል ጋር የተፈራረምኩት የቻርተርፓርቲ ውል የለንም በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ አንደኛ ተከሳሽ (አመልካች) በሐሰት በተዘጋጀ የቻርተርፓርቲ ቢል ኦፍሌድንግ ለባንክ አቀርቦ የወሰደውን የእቃውን ዋጋና የማስጫኛ ዋጋ ለባንክ ለኢንሹራንስ ለፋክስ ያወጣነውንና ከእቃው የምናገኘው ትርፍ በድምሩ 372,269(ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ሺ ሁለት መቶ ስልሣ ዘጠኝ) የአሜሪካን ዶላር እንዲከፍል ሁለተኛውም አመልካች የአንድነትና የነጠላ ሐላፊነት ስላለባቸው ከላይ የተገለፀውን ገንዘብ በአንድነትና በነጠላ እንዲከፍል እንዲወሰንልኝ በማለት ክስ አቅርቧል፡፡

አንደኛው አመልካች በተከሳሽነት ቀርቦ በሽያጭ ውሉ መሰረት አንድ ሺ ሜትሪክ ቶን የአርማታ ብረት በቻርተር መርከብ በመጫን የመርከቡን የመጓጓዣያ ዋጋ በመክፈል እቃው በትክክል “ኬም.ቪ.ማረዋ.ኤም” ከተባለች መርከብ ያለጉድለት የተጫነ መሆኑን የሚያረጋግጥ በመርከቡ አዛዥ የፈረመው የጭነት ማስተወቂያ ደረሰኝ (clear on board bill of lading) ለከሳሽ (ተጠሪ) ልኬአለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ የቻርተርፓርቲ ውል የማቅረብ ግዴታ የለብኝም፡፡ የላኩለት የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ ሐሰተኛ ስለመሆኑ ማስረጃ ያላቀረበ ስለሆነ በራሱ ድክመት ለደረሰበት ኪሣራ እኔ ላይ ያላቀረበው ክስ ተገቢነት የለውም በማለት ተከራክሯል፡፡ ሁለተኛ ተከሳሽ (አመልካች) በበኩሉ አንደኛ ተከሳሽ (አመልካች) ውሉን ካልፈፀመ በአንድነትና በነጠላ ኃላፊ ለመሆን የገባሁት ግዴታ የሌለ በመሆኑ ተጠያቂ ልሆን አይገባኝም በማለት ተከራክሯል፡፡

የተጠሪንና የአመልካቾችን ክርክርና ማስረጃ በመጀመሪያ የሰማውና የመዘነው የከፍተኛው ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ(አመልካች) ከከሳሽ (ተጠሪ) ጋር በገባው የውል ግዴታ መሰረት የሸጠውን የአርማታ ብረት “የኤም ቪ ማሪዋ ኤም” ከተባለችው መርከብ ጉድለት በሌለበት ሁኔታ የጫነ መሆኑን በማረጋገጥ በመርከቡ ካፕቴን በባህር ህጉ አንቀጽ 187 ንኡስ አንቀጽ 3 መሰረት “የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ” (clean on bard bill of lading) ያቀረበ ስለሆነ ግዴታውን ተወጥቷል፡፡ የቻርተርፓርቲ ውል የማቅረብ ግዴታ የለበትም ስለዚህ ለቀረበው ክስ በሐላፊነት የሚጠየቅበት ምክንያት የለም በማለት የወሰነ ሲሆን ሁለተኛው ተከሳሽ (አመልካች) አንደኛው ተከሳሽ(አመልካች) ሐላፊነት የሌለበት በመሆኑ ከቀረበበት ክስ ነፃ ነው በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡ Continue reading “ዕቃዎችን በመርከብ ስለማጓጓዝና የቻርተርፓርቲ ስምምነት (ሰ/መ/ቁ. 21776 -ያልታተመ -3 ለ 2 አብላጫ ድምፅ የተወሰነ)”