Tag: administrative legislation

መመሪያ የሌለው መመሪያ

በመርህ ደረጃ ህግ የማውጣት ስልጣን የህግ አውጭው ነው እንላለን እንጂ በተግባር ግን ህግ የሚወጣው በተወካዮች ምክር ቤት ብቻ አይደለም፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በየትም አገር ያለ እውነታ ነው፡፡ በየጊዜው እያደገ ከሚመጣው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስብስብነት የተነሳ ህግ አውጭው ለእያንዳንዷ ችግር መፍትሄ የሚሆን ህግ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በዓይነትና በጥራት ማቅረብ ይሳነዋል፡፡ አንድ የህግ ረቂቅ ውጤት ያለው ህግ ለመሆን ከሚፈጀው ረጅም ጊዜና ዝርዝር የስነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታ አንፃር ህግ አውጭው በየጊዜው ለሚፈጠር ችግር በየጊዜው አዋጅ እያወጣ መፍትሄ ለመስጠት በቂ ግዜ የለውም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮች ልዩ እውቀትን የሚጠይቁ እንደመሆኑ ውስን የሆነው የህግ አውጭው እውቀት፤ የህግ ማውጣት ስልጣን በተግባር በከፊል የተገደበ እንዲሆንና ሌላ አማራጭ እንዲፈልግ ያስገድደዋል፡ ይህ አማራጭ በውክልና ህግ ( Delegated Legislation) ይባላል፡፡ ተግባራዊ ከሆኑት አስፈላጊ ምክንያቶች የተነሳ ህግ አውጭው ከህዝብ የተሰጠውን ህግ የማውጣት ስልጣን በከፊል ቆርሶ ለስራ አስፈፃውና ለአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ይሰጣል፡፡ በዚሁ መሰረት የሚኒስተሮች ምክር ቤት በተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ በሚሰጠው ስልጣን መሰረት ደንብ ይደነግጋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች በውክልና የህግ አውጭነት ስልጣናቸው መመሪያዎችን ያወጣሉ፡፡

ዋነኛ ስልጣኑ ህግ ማስፈፀም የሆነው ስራ አስፈፃሚው የመንግስት አካል በደንብና በመመሪያ የህግ አውጭነት ስልጣን ደርቦ መያዙ ከስልጣን ክፍፍል መርህ ጋር የሚጣረስ ቢሆንም የህግ አውጭው የጊዜና የእውቀት እጥረት እንዲሁም የመንግስት አስተዳደርን ብቁና ውጤታ ከማድረግ አንፃር በተግባር የግድ ሚል እውነታ ሆኗል፡፡ ሆኖም የውክልና ህግ በዚህ እውነታ ብቻ የሚቋጭ ጉዳይ አይደለም፡፡ ያልተገደበ ስልጣን መኖር ለዜጎች መብትና ነፃት መቼም ቢሆን አደገኛነቱ ጥርጥር የለውም፡፡ የውክልና ህግ የአስፈላጊነቱ እውነታ ከዜጎች መብትና ነፃት ጋር እንዲጣጣም ወይም እንዲታረቅ ተግባራዊ የስልጣን መቆጣጠሪያ መሳሪያ እንዲኖር ግድ ይላል፡፡ እንደ የአስተዳደር ህግ ምሁሩ ዌድ አገላለጽ ከዜጎች ላይ ነፃነት ሲቀነስ አብሮ ፍትህ መጨመር አለበት፡፡ የመንግስት ስልጣኑ ሲለጠጥ በዛው ልክ የዜጎች መብትና ነፃነት እየተሸበሸበ ይመጣል፡፡ ስልጣን ሲጨምር ፍትህም አብሮ መጨመር አለበት፡፡ ይህ ማለት ስራ አስፈፃው ተጨማሪ የህግ አውጭነት ስልጣን ሲሰጠው ስልጣኑን በአግባቡና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ስለመገልገሉ የሚያረጋግጥ ይህም ባልሆነ ጊዜ የሚቆጣጠር መሳሪያ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ Continue reading “መመሪያ የሌለው መመሪያ”